በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ መዝገብ በተከሰሱት ላይ ብይን ሳይሰጥ ቀረ

ሐምሌ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ አመራሮች የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ሀብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሺበሽን ጨምሮ 10 ተከሳሾች ሐምሌ 1/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ብይኑን ሳይሰጥ ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል በጽሑፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር እንደተያያዘለት ገልጾ፣ ነገር ግን ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት አቃቤ ህግ አለኝ ስላለው ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ ጉዳይ ያቀረቡትን መቃወሚያ መርምሮ ብይን ስላልሰጠበት ዋናው ጉዳይ ላይ ለመበየን አለመቻሉን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
ተከሳሾች ባቀረቡት የተጨማሪ ሰነድ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለነገ ሐምሌ 2/2007 ቀጠሮ መስጠቱንም ጋዜጣው ዘግቧል።
በሌላ በኩል ችሎት ደፍራችሁዋል የተባሉት አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና የሺዋስ አሰፋ በቃሊቲ እስር ቤት አያያዝ ላይ ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ህክምና እያገኘ እንዳልሆነና ምክንያቱ ሳይገለጽለት ጠያቂ እንደተከለከለ በመጥቀስ አቤቱታውን ቢያሰማም ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ በጽሑፍ ይዘህ ቅረብ የሚል ምላሽ ሲሰጥ፣ ዳንኤል በበኩሉ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ቸልተኛ የሚሆን ከሆነማ አቤቱታየን አንስቻለሁ ብሏል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ከዞን 9 ጦማርያንና ጋዜጠኞች መካከል 5ቱ መፈታታቸው ተሰምቷል። ጸሃፊ ዘላለም ክብረት፣ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ ፣ ኤዶም ካሳየና ማህሌት ፋንታሁን ክሳቸው ተቋርጦ ተፈተዋል። የቀሪዎቹ 5ቱ ተከሳሾች ክሳቸው እንደሚቀጥል የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።