ኢሳት ዜና (ሰኔ 28 2007 አም)
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የአንድ አመት የእስር ቤት ቆይታ ሲከታተል የቆየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የካሳ ክፍያ በመፈጸም አቶ አንዳርጋቸውን በአስችኳይ እንዲፈታ ማሳሰቡን አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘገቡ።
ባለስምንት ገጽ ውሳኔውን በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በኩል ለኢትዮጵያ ያቀረበው ድርጅቱ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቤት ቆየታቸው ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰባዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው መግለጹን ዘ-ፋይናንሺያል ኤክስፕረስ የተሰኘ
ጋዜጣ ዘግቧል። በድርጅቱ የስቃይ ሰለባ ግለሰቦችን ጉዳይ የሚከታተል ገለልተኛ አካል የአቶ አንዳርጋቸውን የእስር ቤት ሁኔታ ሲከታተል ከቆየ በኋላ ጥሪውን ማቅረቡን ጋዜጣው አመልክቷል።
አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተፈተው ወደ መኖሪያ ሀገራቸው ብሪታኒያ ከመመለሳቸውም በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በቂ የካሳ ክፍያን መፈጸም እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በውሳኔው ገልጿል ።
በቅርቡ የብሪታኒያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በአⶆ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ሲፈጸሙ የቆዩ ኢ-ሰባዊ ድርጊቶችን ይፋ ማድረግ ተከትሎ በርካታ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስጋታቸውን በአዲስ መልክ በመግለጽ ላይ ናቸው ።
የብሪታንያ መንግስት ያሳየው ዲፕሎማሲያዊ መለሳለስ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር አለመፈታት ምክኒያት ሆኗል ሲሉ ድርጅቶቹ ተቃውሞአቸውን እንደገለጹ ዘ-ፋይናንሺያል ኤክስፕረስ ጋዜጣ ዘግቧል።
የብሪታኒያ መንግስት ጠንካራ አቋም ማሳየት መጀመሩን የዘገበው የእንግሊዝ ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ በበኩሉ የሀገሪቱ የፖርላማ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሀገሪቱ የተባበሩት መንግስት ድርጅት አይነትን አቋም እንድትወስድ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ዘግቧል::
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊሊፕ ሀሞንድ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ትብብርን የማያሳይ ከሆነ የሀገሪቱ ግንኙነት ሊሻክር እንደሚችል ማሳሰባቸው ይታወሳል:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ላስተላለፈው ውሳኔ እስካሁን ከኢትዩጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም::