ኢህአዴግ ዲያስፖራውን ለመያዝ ያደረገው ጥረት መክሸፉን ተከትሎ አዳዳስ ስልቶችን እየቀየሰ ነው

ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ዲያስፖራውን በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ለመያዝ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት መክሸፉን ተከትሎ ፣ የዲያስፖራውን ቀልብ ሊስቡ ይችላሉ ያላቸውን አዳዲስ ዘዴዎች እያሰላሰለ ነው።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የዲያስፖራ ሳምንት ዝግጅት ዙሪያ አስመልክቶ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በክልልና በፌደራል ደረጃ ከሚገኙ የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊዎች ጋር ባካሄደው ውይይት ፣ በዲያስፖራው በኩል ይታያሉ የተባሉ በርካታ ችግሮች ተዘርዝረው ቀርበዋል።
የትግራይ ክልል የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ገብረመድህን፣ ” ከፍተኛ ወጪ አውጥተን የትግራይ ዲያስፖራዎች /ተጋሩ ዲያስፖራ/ መቀሌ እና አዲስ አበባን ያካለለ የጉብኝት እና የትሃድሶ ፕሮግራም ብናዘጋጅላቸውም የወጣውን ወጪ የሚተካ አንድም የልማት አጋር ማግኘት ሳንችል ቀርተናል ብለዋል።
በመቀሌ እና አዲስ አበባ ቦታ ለማግኘት ከተመዘገበው ነዋሪ እያስቀደምን የቤት መስሪያ ቦታ እየቆረስን ብንሰጣቸውም፣ በአንድ ጊዜ ሰርተው ሊልኩ የሚችሉትን የቦታ ክፍያ ወደ ቤተሰቦቻቸው አዛውረውት ሂደዋል ሲሉ አክለዋል።
ትግራይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለዲያስፖራ ምቹ የልማት ቦታ ባይሆን እንኳን፣ የትግራይ ዲያስፖራ የሪል ስቴት ግንባታ ማካሄድ ይችል ነበር ያሉት ባለስልጣኑ፣ የእኛ ዲያስፖራ እንደ እስራኤል በበረሃ ማልማትን አለተማረም ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
አቶ አብርሃም በአክሱም ብቻ 23 የሚደርሱ የትግራይ ተወላጅ ዲያስፖራዎች በሆቴል ሎጅ እና ቱሪዝም ለመሰማራት መሬት ቢወስዱም ስኬታማ የሆነ ስራ መስራት አልቻሉም ብለዋል።
በኤምባሲዎች የተመደቡ ዲፕሎማቶች ከዲያስፖራው ጋር ተቀራርበው እንደማይሰሩ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ኤምባሲዎቹና የቆንፅላ ፅህፈት ቤቶቹ የሐበሻ ማህበረሰብ ባለበት አካባቢ ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይገባችሁዋል ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፌይሰል አሊይ ኤምባሲዎችና ቆንፅላ ጽህፈት ቤቶች ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በቋሚነት የሚገናኙባቸው መድረኮች እስካሁን አለመፈጠራቸውንና ለወደፊቱ እንዲፈጠርና በጋራ ተቀራርበው እንዲሰሩ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ በሪፖርታቸው ዲያስፖራውን በተመለከተ ክልሎች መረጃዎችን በወቅቱ አጠናክሮ የመላክ ችግሮች አሉባቸው ያሉ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አንዳንድ መመሪያዎችን በአፋጣኝ ተቀብሎ ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ችግሮች አሉ ሲሉ ወቅሰዋል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ መኮንን በ2007 በጀት አመት ለአባይ ግድብ ግንባታ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ 6 ሚሊዮን 744 ሺ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል። ይህ ገቢ በውጭ ከሚኖረው 2 ሚሊዮን 500 ሺ ህዝብ ጋር ሲነጻጻር ኢምንት ነው።
ኢህአዴግ የዲያስፖራ ቀን በሚል ከነሐሴ 4-10 ድረስ ለማክበር አቅዷል። ወደ አዲስ አበባ ለሚሄዱ ዲያስፖራዎች፣ ከኢምባሲ የድጋፍ ደብዳቤ ካመጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 50 በመቶ ቅናሽ ያደርግላቸዋል። ኦሮምያ ክልል ደግሞ ለበአሉ ለሚሄዱ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች የሆቴል ወጪ እንደሚሽፍን መረጃዎች ያመለክታሉ።