ባለፉት ሶስት አመታት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የውጭ ፕሮጀክቶች ውስጥ አብዛኞቹ ተሰረዙ

ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለሚቀጥለው አምስት አመታት ይተገበራል ተብሎ በተዘጋጀ የሁለተኛ ዙር የ5 አመታት እቅድ ላይ በተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ እንደተመለከተው ባለፉት ሶስት አመታት 2 ሺ 995 ፕሮጀክቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ስኬታማ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ተሰርዘዋል።
በአማራ ክልል በባህርዳር እንዲሁም በኦሮምያ ክልል አዳማ የተደረገውን የምክክር ጉባኤ አስመልከቶ የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያሳየው፣ በዚህ አመት ወደ አገር ውስጥ ከገቡና መምረት ከጀመሩ 166 ፕሮጀክቶች መካከል ውጤታማ መሆን የቻሉት አምስት ብቻ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ለስራቸው ማንቀሳቀሻ የሚሆን 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወጪ ያደረጉ ሲሆን፣ ከ31ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎችም ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ በግንባታ ደረጃ ላይ ያሉ 351 ፕሮጀክቶች ለ72ሺ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል ሲባል በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን የተላለፈው ዜና እና ሪፖርት በስህተት መሆኑን በውይይቱ ተነስቷል።
የሪፖርቶች የተአማኒነት ችግር ስርአቱን እየፈተነው መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።
በማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ካወጡ 272 የውጭ አገር ድርጅቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከስረው መዘጋታቸውን ፣ 59 በግብርና፣ 230 ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ አውጥተው እስካሁን ስራ አለመጀመራቸው በሰነዱ ተመልክቷል።
ሃገሪቷ የምታመርተው ምርት ጥራት፣ መጠንና በአለም ገበያ ውስጥ ሰብሮ የመግባት አቅም ሲመዘን ከአመት አመት እወደቀ እና በሌሎች ሀገራት እየተበለጠች መምጣቷን የሚያወሳው የውይይት ሰነዱ በምክንያትነት ያስቀመጠውም፣ የሊብራል ሃይሎች በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ላይ ያላቸው ጥላቻ እና ከቻይና ጋር ባላት ወዳጅነት የሚል ነው፡፡