በከፍተኛ ድጎማ ከውጪ የተገዛ ስንዴ ለህዝቡ መከፋፈል መጀመሩን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ

ኢሳት ዜና:- አቶ መለስ ዜናዊ ባለፉት 20  አመታት የእርሻ ምርት በ40 በመቶ ማደጉን በገለፁበት ማግስት በከፍተኛ ድጎማ ከውጪ የተገዛ ስንዴ ለህዝቡ መከፋፈል መጀመሩን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ። በስንዴ እጥረት ምክንያት፡በርካታ ዳቦ ቤቶች ሥራቸውን ባቆሙበት ባሁኑ ጊዜ መንግስት ለአንድ ኩንታል እስከ ሁለት መቶ ብር ድጎማ በማድረግ  ከውጪ የገዛው ስንዴ በዐዲስ አበባ በሁሉም ወረዳዎች እየተከፋፈለ ነው።

ስንዴው እታደለ  ያለውበ ሸማቾች ማህበር አማካይነት ሲሆን አንድ ቤተሰብ 275 ብር በመክፈል 50 ኪሎ  እንዲወስድ ይደረጋል። እንደ ኢቲቪ ዘገባ ፤አንድ ቤተሰብ ስንዴ ከመውሰዱ በፊት የቀበሌ መታወቂያ ማሳየት   አለበት።

ከተለያዩ ክልሎችና ገጠሮች ለስራ ፍለጋና  በችግር ምክንያት እጅግ በርካታ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ ቢሆንም፤ የቀበሌ መታወቂያ ስለማይኖራቸው የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ታውቋል።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ-ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሪ ሀላፊ አቶ አብደላ ኡመር፤ ሰው ይሄን ስንዴ ሲያገኝ መሰረታዊ ፍላጎቱን ያሟላል ለአምባሻ ይጠቀምበታል። ህዝቡም እየጠየቀ ያለው፤
ስንዴው ይሰጠን እቤታችን ዳቦውን እንጋግራለን እያለ ነው። እኛም ጥያቄውን እየመለስን ነው” ብለዋል።

ይሁንና የኑሮ ውድነት  በሁሉም ዘርፍ ጣራ በነካበት በአሁኑ ጊዜ ለአንድ ቤተሰብ በ 275 ብር 50 ኩንታል ስንዴ በመታደሉ  ሀላፊው የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎት ይሟላል ማለታቸው  ታዛቢዎችን
ያስገረመ ሆኗል።

እንዲሁም መንግስት 11 በመቶ እድገት አስመዘገብኩ እያለ ባለበት ሰዓት  በረሽን መልክ ስንዴን ማከፋፈሉን፤ የመንግስት መገናኛ ብዙሀንን  እንደ አንድ  ታላቅ የልማት ድልና ስኬት  ከሚመስል አቅጣጫ እያጋነኑ ማቅረባቸው፤  የኢህአዴግ መንግስት፤ የዕድገት ዲስኩር  ዳርቻና ጥግ የት ድረስ እንደሆነ በግልፅ የሚጠቁም ነው ሲሉ እነኚሁ ወገኖች ተናግረዋል።