ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ብር ወጪ ይሰራል የተባለውን የመለስ ፋውንዴሽን ለማስገንባት ህዝቡ በፈቃደኝነት ገንዘብ ያዋጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ የህዝቡ መልስ አስደንጋጭ መሆኑን የተረዳው በወ/ሮ አዜብ መስፍን የሚመራው ፋውንዴሽን፣ የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም የመንግስት ደሞዝ ተከፋይ ሁሉ ገንዘብ እንዲያዋጣ ለማስገደድ ሞክረዋል። ግምገማ በመፍራትና በግዳጅ ገንዘብ እንዲያዋጡ ከተደረጉት መካከል የመከላከያ ሰራዊት አባላት ይገኙበታል። የሰራዊቱ አባላት እንደሚናገሩት በወር የሚከፈላቸው ክፍያ አነስተኛ ቢሆንም፣ ለአባይ ግድብ ማሰሪያና እና ለመሳሰሉት በቋሚነት እየከፈሉ አሁን ደግሞ ለመለስ ፋውንዴሽን በግዳጅ እንዲከፍሉ ተገደዋል። የመለስ ፋውንዴሽንን ያልከፈለ የሰራዊት አባል ከፈትኛ ችግር እንደሚገጥመው አባላቱ ይናገራሉ።
አስገድዶ የማስከፈሉን ስራ ወደ ሲቪል ሰርሲስ ሰራተኛው ለማውረድ የተደረገው ሙከራ ግን በሰራተኛው ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሊሳካ አልቻለም።
በአንዳንድ የማግባቢያ መድረኮች ላይ “ለአባይ ካዋጣን ይበቃናል” የሚሉ ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ሙሉ ለሙሉ ስሙና ተቋማዊ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ እንደሚቀየር ታውቋል። አዲሱ ስያሜው የመለስ ዜናዊ የስልጠና እና የምርምር አካዳሚ እንደሚባል ከመስተዳደሩ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ተቋሙ ከ1991 ዓም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለረጅም ዓመት በስራ ዓመራር መስክ አጫጭር ስልጠና እንዲሁም ሌሎች የስልጠና ዘርፎች ላይ በማተኮር የሙያ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ካለፉት 3 ወራት ጀምሮ ተቋሙን ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፣በአዲስ መልክ የዘመናዊ ኢንተርኔት መስመር ዝርጋታ፤ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ከ150-200 የሚደርሱ የስለላ ካሜራዎች ተከላና ሌሎችም ሰፋፊ ስራዎች በከፍተኛ ወጪ ተስርቷል።
95 በመቶ የሚሆኑ ነባር የተቋሙን አጠቃላይ ሠራተኞች በማስወጣት መቶ በመቶ የህወሃት አባላት በሆኑ ሠራተኞች ብቻ ለመተካት እንቅስቃሴ መጀመሩ እንዳስገረማቸው የመስተዳድሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ ላሉ የትምህርት መስኮች ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ማስልጠኛ እና ሌሎች ከፍተኛ የኢህአዴግ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሰነዶች ማምረቻ፣ እንዲሁም የኢንተርኔት መረጃ መረብ የስለላ ተቋም በመሆን ለማገልገል ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው። ለሠራተኞች የሚከፈለው ደሞዝ በአንፃራዊነት ከሌሎች የሃገሪቱ ተቋማት የደመወዝ መክፈያ ስኬል የተሻለ እንደሆነ ታውቋል።
ህወሃት የትግል ታሪኩን በህዝቡ ውስጥ አስርጎ ለማስገባት እንዲሁም የመለስ አስተምህሮ በሃገሪቱ ውስጥ በስፋት እንዲሰራጭ ለማድረግ ተቋሙ ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 14/1991 ዓ.ም የከተማ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ተቋሙ በጀት የሚያገኘው ከመንግስት ይሁን እንጅ፣ በአዲስ ከተዋቀረ በሁዋላ ግን ስልጠናውን የሚሰጠው ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ነው።
በአቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራው የኢህአዴግ የከፍተኛ አመራሮች ማሰልጠኛ ተቋም የመለስ ዜናዊ ማሰልጠኛ ተቋም የተባለ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ስያሜም እንዲሁ በመለስ ስም እንዲቀየር መወሰኑ የመስተዳድሩን ሰራተኞች አነጋግሯል። በክልል ደግሞ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችና መጽሃፍት ቤቶች በመለስ ዜናዊ ስም እየተሰየሙ ነው። የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽንም ሲጠናቀቅ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ስም ይይዛል።