በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ነው

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሳምንት በፊት አልሸባብ የተባለው የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል በቡርካባ ግዛት ጃሚዮ በሚባል ቦታ ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ ከ30 በላይ ወታደሮችን ከገደለ በሁዋላ፣
በርካታ ቁስለኞች ሞቃዲሹ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ቁጥር ሁለት ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው በመታከም ላይ ናቸው።
አሚሶም በመባል የሚታወቀው በሶማሊያ የሰፈረው የአፍሪካ ህብረት ጦር በአልሸባብ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዟል። የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተወካይ ሊዲያ ዋንዮቶ በሆስፒታሉ የተኙትን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጎብኝተዋል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት አንድ ቁስለኛ ወታደር ” በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በጋራ እየተጓዝን በነበረበት ወቅት ተኩስ ከፈቱብን። ጦርነቱም ከሰአት በሁዋላ ከ11 ሰአት እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ቆየ ። የአልሸባብ ወታደሮች የተለያዩ የጦር
መሳሪያዎችን ይዘው ነበር ። የውጭ አገር ተዋጊዎችም አብረዋቸው ነበሩ” ብሎአል።
አሚሶም ጥቃቱን ማክሸፉን በመግለጫው ጠቅሷል። የአሜሶም ቁጥር 3 አዛዥ ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ሚሊሺያዎቹ በወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክሩም የአፍሪካ ህብረትና የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች አሸንፈዋቸዋል
ብለዋል።
አልሸባብ በሶማሊያ ውስጥ ሰላም እንደሌለ ለማስመሰልና በህዝቡ ዘንድ ፍርሃት ለመልቀቅ ብሎ የወሰደው እርምጃ ነው ሲሉ ኮሎኔሉ ተናግረዋል። የኢህአዴግ መንግስት በወታደሮቹ ላይ ስለፈጸመው ጥቃት እስካሁን መግለጫ አልሰጠም።