ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን ተሻግረው በሽበርተኝነት የተፈረጀውን የግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ሲሉ ማይካድራ ላይ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ያላቸውን
እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።
ዛሬ ሰኔ 9/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የቀረቡት በእነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የክስ መዝገብ የተካተቱት አራት ተከሳሾች ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ ናቸው።
ተከሳሾቹ ጠበቃ ማቆም አንፈልግም በማለታቸው ያለጠበቃ የቀረቡ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በክስ መቃወሚያቸው ላይ ሁለት አብይት ነጥቦችን በመጥቀስ ክሱ ውድቅ ተደርጎ በነጻ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ክስ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጣረስና በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት ያልቀረበ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ በማድረግ በነጻ ሊያሰናብተን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች በቀረበው አቤቱታ ላይ አቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥ በሚል ለሰኔ 19/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አንደኛ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ በተደጋጋሚ በእስር ቤት በሚደርስበት በደል ላይ አቤቱታ
ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ አቶ ብርሃኑ አለኝ የሚለውን አቤቱታ በጽሑፍ እንዲያቀርብ አዝዞ የነበር ቢሆንም አቶ ብርሃኑ የማዘጋጀውን አቤቱታ ‹‹እንዴት ማረሚያ ቤቱን ትከሳለህ?›› በሚል ጽሑፉን እየተነጠቀ እንደሆነ
በመግለጽ አቤቱታውን በጽሑፍ ማቅረብ እንዳልቻለ አስረድቷል፡፡
ይህን የአቶ ብርሃኑን አቤቱታ በተመለከተ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ተደርገው ”ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያለውን አቤቱታ እንዲያቀርብ አዝዘናል፤ ስለዚህ እናንተ መልስ ካላችሁ መልሳችሁን እንቀበላለን፣ አሁን ግን
ተከሳሹ የሚያዘጋጀውን አቤቱታ እንዲያቀርብ አድርጉ›› በማለት ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፏል። በመሆኑም አቶ ብርሃኑ በቀጣዩ ቀጠሮ በእስር ቤት አያያዝ ላይ ያለውን አቤቱታ በጽሑፍ ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ነገረ
ኢትዮጵያ ዘግቧል።