ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ቅዳሜ በሰሜን ጎንደር ዞን በጭልጋ ከተማ የፌደራል ፖሊሶች በወዱት እርምጃ ከ5 እስከ 6 የሚደርሱ ወጣቶች መገደላቸውን፣ ከ10 ያላነሱ ወጣቶች ደግሞ መቁሳላቸውን የአይን
እማኞች ገልጸዋል።
የቅማንት ተወላጆች የራስ አስተዳደር መብት ይሰጠን በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት “ጥያቄያቸው በክልሉ ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ሌሎች ብሄረሰቦች ሊታይላቸው” ይገባል የሚል ውሳኔ አሳልፏል። ጥያቄ አቅራቢዎቹ የራስ አስተዳደሩ በ120 ቀበሌዎች ተግባራዊ እንዲሆን ሲጠይቁ፣ የክልሉ መስተዳደር በበኩሉ ውሳኔውን የሰጠሁት ለ42 ቀበሌዎች ብቻ ነው ብሎአል። የመስተዳደሩን ውሳኔ በመቃወም ፣ ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴው ሰኔ 7 ጭልጋ ላይ፣ ሰኔ 14 ደግሞ
ጎንደር ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢጠራም፣ የሰሜን ጎንደር ዞን መስተዳደር ከአስተባባሪ ኮሚቴው የቀረበለትን የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ጥያቄ ውድቅ በማድረግና ኮሚቴው መፍረሱን በመግለጽ ምላሽ ደብዳቤ ልኳል።
የኮሚቴው አባላትና ደጋፊዎች የመስተዳደሩን ማስፈራሪያ ወደ ጎን በመተው ባለፈው ቅዳሜ ቅስቀሳ ለማድረግ በጭልጋ ከተማ ተንቀሳቅሰዋል። ከአርማጭሆ ወረዳ የመጡ የብሄረሰቡን የባህል ልብስ የለበሱ 7 ወጣቶችን ፖሊስ በመኪና ጭኖ
በመውሰዱ ግጭት መጀመሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአካባቢው በሚታየው ውጥረት የተነሳ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡንም ነዋሪዎች ይናገራሉ።