ግንቦት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዋና ኦዲተር የ2006 ዓ.ም የመንግስት መ/ቤቶች የሂሳብ ሪፖርት ትላንት ለፓርላማው ያቀረበ ሲሆን በዚህ ሪፖርቱ ያለምንም ማስረጃ ገንዘብ ያወጡ 19 መንግስታዊ ተቋማት የተገኙ
ሲሆን እነዚህ ተቋማት በድምሩ ከ473 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አውጥተው ተገኝተዋል፡፡
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ላቅ ያለውን ድርሻ ማለትም 274 ሚሊየን ብር ያወጣው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በቀጣይም በምክትል ጠ/ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ የሚመራው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር
111 ሚሊየን ብር፣ መቱ ዩኒቨርሲቲ 16 ሚሊየን ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 12 ሚሊየን ብር፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 10 ሚሊየን ብር ወጪ አውጥተው ተገኝተዋል፡፡
ዋና ኦዲተር በዚህ ወጪ ላይ በሰጠው አስተያየት ማስረጃ ያልቀረበለት ሂሳብ በቂ ማስረጃ እንዲቀርብበት ያሳሰበ ሲሆን አለበለዚያ ገንዘቡ ወደመንግስት ካዝና እንዲመለስ አዟል፡፡
ዋና ኦዲተር አያይዞም ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ78 መ/ቤቶች ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ በደንቡ መሰረት ሳይወራረድ መገኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በወቅቱ ሂሳብ ከማያወራርዱት ተቋማት መካከል መከላከያ ሚኒስቴር
144. 2 ሚሊየን ብር፣ ፌዴራል ፖሊስ 64. 4 ሚሊየን ብር ድርሻ ወስደዋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ ለዚህ የአሰራር ክፍተት በሰጠው አስተያየት ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደሐብት የመለወጥ ዕድሉ ተዳክሞ ለብክነት በር የሚከፍት በመሆኑ መ/ቤቶቹ የፋይናንስ
ደንብና መመሪያዎችን ተከትለው እንዲሰበስቡና እንዲያወራርዱ ወይም ከመዝገብ እንዲሰርዙ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
ዋና ኦዲተር በዚህ ሪፖርቱ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ 47 መ/ቤቶች ከ53 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸማቸውን አረጋግጧል፡፡ እነዚህም ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማለትም ጅማ፣ ባህርዳር፣ ዲላ፣ ሐዋሳ፣ አርባምንጭ፣
ወላይታ ሶዶ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙበት ሲሆን ዋና ኦዲተር መ/ቤቶቹ አለአግባብ የፈጸሙትን ክፍያ እንዲመልሱ በሪፖርቱ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ዋና ኦዲተር በእያመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሂሳብ አያያዝ ደንብን ባልተከተለ መንገድ መውጣቱን ለፓርላማ ቢያቀርብም፣ ሪፖርቱን መሰረት አድርጎ የክትትል ስራ አይሰራም። በዚህም የተነሳ በያመቱ ከፍተኛ ገንዘብ በሙስና ስም ይባክናል።