ግንቦት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ለኢሳት በላከው መግለጫ ፣የኦብነግ ሁለቱ ተደራዳሪዎች አቶ ሱሉብ አህመድና አቶ አሊ ሁሴን ፣ እኤአ ሰኔ 1 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የደህንነት
ባለስልጣን አጃቢነት የኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ከተማ የሆነችው ሞያሌ ደርሰዋል። ሁለቱ ልኡካኖች ናይሮቢ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተዋል። ኦብነግ ተወካዮቹ በኬንያ መንግስት እና በአለማቀፍ ማህበረሰብ ጥረት መለቀቃቸውን ገልጾ ፣
ከመንግስት ጋር ለሚደረገው ድርድር አንድ እንቅፋት የነበረው ችግር መነሳቱን ገልጿል። የኬንያ መንግስት ኦብነግና መንግስትን ለማደራደር እየጣረ መሆኑንም ግንባሩ በመግለጫው አስታውቋል።
አንዳንድ የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት በስልጣን ላይ ያሉትን የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድን በአካባቢው የተሻለ ተቀባይነት ባላቸው ሰዎች የመተካት ፍላጎት አላቸው። ከኦብነግ ጋር የሚደረገው ድርድር ከተሳካ በስልጣን ላይ ያሉት አቶ አብዲ ቦታቸውን ሊያስረክቡ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።