ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እንደ አዲስ ስታንዳርድ ዘገባ እየተካሄደ ባለው ዓመታዊው የባንኩ የቦርድ ስብሰባ ላይ ነው ለፕሬዚዳንትነቱ ሲወዳደሩ ከነበሩት ስምንት ዕጩዎች መካከል የገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፊያን አህመድ የሴራውሊዮኗን ሳሞራ ሚሸል ካማራን ተከትለው ሁለተኛው ተሰናባች ሆነዋል።
ቦርዱ እንደ አውሮፓያኑ አቆጣጠር ባለፈው ፌብሩዋሪ 11 ቀን አቢጃን በሚገኘው የባንኩ ዋና ጽህፈት ቤት ባደረገው ስብሰባ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትርን ጨምሮ ስምንት ስዎች በእጩነት መቅረባቸው ይታወቃል።
ይህም የሆነው አቶ ሶፊያንና ሌሎቹ ዕጩዎች ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሩዋንዳ-ኪጋሊ በተካሄደው የባንኩ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ለመሆን እንደሚፈልጉ ፍንጪ በማሳየታቸው ነበር።
ላለፉት አስር አመታት ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ዶናልድ ካቤሩካ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።
ጋዜጣው እንደዘገበው የተለያዩ አገር መንግስታት በእጩነት የቀረቡት ዜጎቻቸው እንዲመረጡ ቅስቀሳ ቢያደርጉም ፣ የኢህአዴግ መንግስት ግን ለአቶ ሶፍያን ቅስቀሳ አላደረገም። መንግስት ለአቶ ሶፍያን ቅስቀሳ ለማድረግ ለምን እንዳልፈለገ የገለጸው
ነገር የለም። አቶ ሶፍያን ለአፍሪካ ህብረት መወደዳራቸው በመጪው ጊዜ በስልጣን ላይ እንደማይቆዩ አመላካች ሆኗል።