አለም አቀፍ ስደተኞች ተቋም ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ወደአገራቸዉ አጓጓዘ

ኢሳት ዜና ግንቦት 18 2007

በየመን መዉጫ አጥተዉ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን መካከል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸዉን ጨምሮ ከሁለት እሺ በላይ ሰደተኞችን ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ማጓጓዙን አለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ገለጠ።

ድርጅቱ የሳዉዲ አረቢያ፥ ሱዳንና፥ ጂቡቲን የድንበር ግዛት በመጠቀም ስደተኞቹን ወደአገራቸዉ መመለስ መቻሉን አስታዉቋል።

በየመን መዉጫን አጥተዉ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መንግስት ዜጎችን ለመታደግ በቂ ጥረት አላደረገም ሲሉ ቅሬታቸዉን ሲገልጹ መቆየታቸዉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያዉያኑን የድረሱልን ጥያቄ ተከትሎም የዓለምአቀፉ የስደተኞች ተቋም (International Organization for Migration) ከየመን ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ስደተኛ ኢትዮጵያኑን ለማስወጣት ዘመቻ መጀመሩን ይገልጻል።

በየመን ሲፈጸም በነበረ የአየር ጥቃት ጉዳት ደርሶባት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰች አንዲት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ በርካታ ኢትዮጵያዉያን አሁንም ድረስ ከየመን መዉጫ ኣጥተዉ እንደሚገኙ ተናግራለች።

በተጨማሪ ከ2000 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሀገራቸዉ ለመመለስ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘዉ  አለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥያቄዉን አቅርቧል።

በጅቡቲ የሚገኘዉ የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ቢሮ (IOM) በየመን ሃራድ መዉጫን አጥተው የሚገኙ 565 ኢትዮጵያዉያንን ለማስወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በየመን ሰነዓ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ አካላትን ለደህንነታቸዉ ሲል ማስወጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያዉያን አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ እንደሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በየመንና በሊቢያ መዉጫን አጥተው ለሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በቂ ትኩረት አልሰጠም በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተቃዉሞቸዉን በአደባባይ መግለጻቸዉ የሚታወስ ሲሆን የፀጥታ ሃይሎችም የሃይል እርምጃን በመዉሰድ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዉለዋል።