በእሁዱ ምርጫ ላይ ታዛቢዎችና መራጮች ትዝብታቸውን እየተናገሩ ነው

ሚያዝያ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው እሁድ ግንቦት15 ፣ 2007 ዓም የተካሄደው ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንደተካሄደ መንግስትና ብቸኛው የውጭ ታዛቢ የአፍሪካ ህብረት ቢገልጽም፣ በምርጫው የተሳተፉ ታዛቢዎችና መራጮች ምርጫው በአሳዛኝ ሁኔታ መካሄዱን መስክርነታቸውን እየሰጡ ነው።
በአዲስ አበባ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢ የነበረው አቶ መሰለ አድማሴ እንደገለጹት እርሳቸው በታዘቡበት የምርጫ ጣቢያ፣ የምርጫ ኮሮጆዎች ታዛቢዎች ሳይገኙ መከፈታቸውን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ካርድ ሲያስገቡ ማየታቸውንና ለምን ሲባሉ ” ለአባቴ ነው የምመርጠው” የሚል መልስ መስጠታቸውን እንዲሁም የደህንነት ሃይሎች ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ገብተው ሲያስፈራሩ መታዘባቸውን ተናግረዋል

በኦሮምያ ክልል በአወዳይ ከተማ በነበረው ምርጫ ደግሞ ለመራጮች የኢህአዴግ ወረቀት ብቻ ተባዝቶ እንደተሰጣቸውና ለምን ብለው የጠቁ ሰዎች በፖሊሶች መያዛቸውን ታዛቢዎች ተናግረዋል ። ምርጫውን የልጆች ጨዋታ ነበር ሲሉ ያጣጣሉት ታዛቢዎች በምርጫ ለውጥ ይመጣል የሚለው ተስፋቸው እንደተሟጠጠ ተናግረዋል

“በጣም አስገራሚ ነው” የሚሉት ሌላው ታዛቢ ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ፍተሻ በሚያደርጉበት ወቅት ” ኢህአዴግን” ምረጡ ከማለት ጀምሮ፣ ሌላ ፓርቲ ሲመርጡ ያዩዋቸውን ወጣቶች ተከታትለው መያዛቸውን ገልጸዋል።
በባህርዳር ደግሞ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ሰማያዊ ፓርቲ የተሻለ ድምጽ በማግኘቱ የብአዴን ባለስልጣናት ከትናንት ጀምረው ግምገማ እያደረጉ ነው። የግምገማው አላማ ሰማያዊ በ4 ጣቢያዎች እንዴት ይህን ያክል ድምጽ ሊያገኝ ቻለ የሚል ሲሆን፣ ምርጫውን ሲያስፈጽሙ በነበሩት ላይ ምርመራ እንደሚካሄድባቸው ምንጮች ገልጸዋል።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በግል ከሚሰጡዋቸው አስተያየቶች ውጭ እስካሁን በይፋ መግለጫ ባይሰጡም
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዓለማቀፍ ድጋፍ ሰጭ ቡድን <<የህዝብ ድምፅ ዝርፊያ እና የምርጫ ማጭበርበር ተከትሎ ለሚነሳው የህዝብ ተቃውሞም ሆነ መንግሥት ለወሰደው እና ለሚወስደው እርምጃ ተጠያቂው እራሱ ኢሓዴግ ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል። <<ወያኔ በምርጫው ቅስቀሳ ሂደት ድብደባ፣ አፈና ፣እስራት ፣ግድያ እና እንግልት በግልጽ ፈጽሟል::>>ያለው ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳቀኝ እና በአርሲ ኮፈሌ የተፈጸመው ግድያ ፤ በእነ በቀለ ገርባ ላይ በበደሌ ላይ በጅማ እና በነቀምቴ የተፈጸመውን ድብደባ ” ለአብነት አንስቷል።
የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተስፋ መቁረጣቸውን ተከትሎ ለምርጫው ሁለት ቀናት ሲቀሩት ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማው በማይጠራበት ወቅት ስብሰባ በመጥራት ማስፈራሪያ እና ዛቻ በተቃዋሚዎች ላይ ሰንዝረዋል ያለው የ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄ ድጋፍ ሰጪ ቡድን፤ ይህም አስቀድሞ የምርጫውን ውጤት ለመቀልበስና በሃይል ምርጫውን ለማጭበርበር ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር የሚያስይ ነው ብሏል።
የኢሕዴግ ካድሬዎች የምርጫው ዋዜማ ሌሊት ከአለቆቻቸው የተላለፈውን ትእዛዝ ለመፈጸም አስቀድመው ኮሮጆ በመሙላትና በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የፌዴራል ፖሊሶችን፣ ሚሊሺያዎችን፣ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶችን እና አድማ በታኝ ፖሊሶችን በማዝመት ሙሉበሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ የምርጫ ቦርድ ተወካዮችን እና የተቃዋሚ የምርጫ ታዛቢዎችን መታወቂያቸውን በመቀማት እያስፈራሩ እየደበደቡ ከምርጫ ጣቢያ በሀይል እንዳባረሩዋቸው ቡድኑ አውስቷል።
በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የምርጫ ካርድ መከልከላቸውንና የመምረጥ መብታቸዉ መነፈጉን የጠቀሰው የ ኦፌኮ ድጋፍ ሰጪ ቡድን፤። ስለሆነም: ፀረ ሠላም እና ፀረ ዴሞክራሲ የሆነው የዘረፋ ቡድን የፈጸመውን ምርጫን የማጭበርበር ፣ የህዝብ ድምፅን የመዝረፍ፣ ንጹሃን ዜጎችን የመግደል እና የማሰር ድርጊት አጥብቆ እንደሚያወግዘው አስታውቋል።
<<. ኦፌኮ/ መድረክ በኦሮሚያ ክልል ምርጫዉን ሙሉ ለሙሉ አሸንፏል፣ የተፈፀመው ድርጊት በማንኛውም አለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት ተቀባይነት የሌለው እና ህገ ወጥ በመሆኑ በጽኑ እናወግዘዋለን: ፡>> የሚለው መግለጫ፤ ይህንን የህዝብ ድምፅ ዝርፊያ እና የምርጫ ማጭበርበር ተከትሎ ለሚነሳው የህዝብ ተቃውሞም ሆነ መንግሥት ለወሰደው እና ለሚወስደው እርምጃ ተጠያቂው እራሱ ኢሓዴግ ነው።>> ብሎአል።
ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ አክሎም ፦”ህዝባችን፤ የመረጠው ድርጅት ኦ.ፌ.ኮ /መድረክ/ የሚያደርገውን ቀጣይ የትግል ጥሪ ህዝቡ ዝግጁ በመሆን እንዲጠብቁ እናሳስባለን “ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የነበረውን ምርጫ ተአማኒ ነበር ሲል ገልጾታል። ህብረቱ በታዛበባቸው 21 ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ባዶ ኮሮጆዎችን ማሳየት አለመቻላቸውንና በአንዳንድ ቦታዎችም የምርጫ ሰአቱ ከመጀመሩ በፊት የምርጫ ጣቢያዎች መከፈታቸውን ገልጿል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና የህብረቱን መግለጫ አጣጥለውታል። የረዩተርሱ አሮን ማሾ እንደዘገበው ደ/ር መረራ እርሳቸው በተወዳደሩባቸው ጣቢያዎች ምርጫው እንደተዘረፈ በመጥቀስ አጠቃላይ ምርጫው ቧልት ነበር ብለዋል።