ሚያዝያ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦም ኤም፣ የመን ውስጥ በችግር ላይ የነበሩ 2061 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው መመለሱን አስታውቋል። ከተመሰሉት መካከል የቆሰሉ ኢትዮጵያውያንም አሉበት።
አይ ኦ ኤም በአዲስ አበባ ጊዚያዊ ማቆያ ጣቢያ ተመላሾችን በማስፈር የትራንስፖርት እና የጤና አገልግሎት መስጠቱን አስታውቋል።
ሃድራ የተባለች ተመላሽ በቤት ሰራተኛነት ስትሰራ እንደነበር ገልጻ፣ የአየር ድብደባ በሚካሄድበት ወቅት አጠገቧ የነበረ ስሊንደር ፈንድቶ ሆስፒታል መግባቷንና ያጠራቀመችው ገንዝብ ሁሉ ለህክምና መዋሉን ተናግራለች። አሁን ድርጅቱ በሰጣት ገንዘብ ወደ ቤቷ ተመልሳ ሁለት ልጆቿን እንደምታገኝ ተስፋ ማድረጓን ገልጻለች።
ሁኔታው በጣም ከባድ ነው የምትለው ሃድራ፣ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ እንደሚፈጸም፣ በመብራት እና ውሃ ችግር ሲሰቃዩ እንደነበር ተናግራለች።
ድርጅቱ እንደሚለው የየመን ግጭት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ 3 ሺ 177 ኢትዮጵያውያን ከየመን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። 2 ሺ 889 የሚሆኑት በሳውድ አረቢያ፣ 250 በካርቱም እንዲሁም 38 በጁቡቲ በኩል ወደአገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል።
አይ ኦ ኤም ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት 250 ሺ ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።
ድርጅቱ ሃራድህ በተባለ የየመን ግዛት ውስጥ መውጫ አጥተው የሚገኙ 565 ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።