ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው መምህር ፍትህ ማጣቱን የሚያትት ደብዳቤ ጽፎ ማለፉ ታወቀ

ሚያዝያ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው አርብ ባሃድያ ዞን በሶሮ ወረዳ በጊምቢቾ ከተማ የፊዚክስ መምህር የነበረው ጌታቸው አብራሃም ፣  በወረዳው አስተዳደር  ግቢ ውስጥ ቤንዚን አርከፍክፎ ራሱን አቃጥሎ ገድሏል።

የመድረክ አባል የነበረው መምህር ጌታቸው ከምርጫው ጋር በተያያዘ የምርጫ ቅስቀሳ ያደርግ ነበር። የተቃዋሚ አባል በመሆኑ ብቻ የ3 ወር ደሞዙን እንዳያገኝ የተከለከለው መምህር፣ አቤቱታውን ለተለያዩ ባለስልጣናት ሲያቀርብ ቆይቷል። በመጨረሻ ተስፋ በመቁረጥ ደብዳቤ

ጽፎና የመድረክን የምርጫ አርማ ከጎኑ አድርጎ በምክር ቤቱ ግቢ ውስጥ ራሱን አቃጥሎ ገድሏል። መምህሩ ራሱን ማቌጠሉን ተከትሎወደ ሆሳእና ሆስፒታል ቢወሰድም ሊተርፍ አልቻለም።

ጓደኞቹ ለኢሳት እንደተናገሩት፣ የ28 አመቱ መምህር ጌታቸው ጤነኛ እና ጥሩ ጸባይ የነበረው ነው። የመምህሩ የቀብር ስነስርአት ባለፈው አርብ በጊምቢቾ ከተማ ተፈጽሟል።

በተመሳሳይ ዜናም በአፋር ክልል ቡሩ ሞዳይቶ ከተማ ላይ ከሰል በማክሰል ይተዳደር የነበረ ነዋሪ፣ የክልሉ ፖሊሶች 50 ሺ ብር የሚያወጣውን ከሰሉን ስላቃጠሉበት ተበሳጭቶ መርዝ በመጠጣት ራሱን አጥፍቷል።

ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደው ሌላው ነጋዴ መትረፉ ሲታወቅ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ቤት መቃጠሉም ታውቋል።

ፖሊሶች ዛፍ ምንጠራን ለመከላከል በሚል ምክንያት እርምጃውን መውሰዳቸው ታውቋል። ነዋሪዎች ፣ መንግስት ደን እንዳይመነጠር ቢፈልግ እንኳ፣ ነጋዴዎች እስካሁን የያዙትን እንዲሸጡ በማድረግ ተጨማሪ ቁጥጥር ማድረግ ይችል ነበር  ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በርካታ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎችና የቀድሞ የህወሃት ጦር ጡረተኞች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ  ደን እየመነጠሩና ከሰል እያከሰሉ ወደ ሱዳን እንደሚልኩ ይታወቃል።