ሚያዝያ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በማምረቻ ወይንም በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ መንግስት በያዘው የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት መከናወን ካለባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል ከሲሚንቶ በስተቀር አለመሳካቱን አንድ ሰነድ አመልክቷል፡፡
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ ሰነድ እንዳመለከተው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም በሚጠናቀቀው የአምስት ኣመት እድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ጥቅም ላይ የዋሉ ወረቀቶችና ከነባር ፋብሪካዎች ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተደምሮ 19 ሺ ቶን የማምረት
አቅም ቢፈጠርም በ2007 ዓ.ም 150 ሺ ቶን ከፐልፕ ወረቀት ለማምረት የተያዘው እቅድ የኢንቨስትመንት ካፒታሉ መጠን ከፍተኛ ነው በሚል ወደ ትግበራ መግባት አልቻለም፡፡
በዓመት 50ሺ ቶን ኮስቲክ ሶዳ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በማቋቋም ከውጭ የሚገቡ የፕላስቲክ ግብዓት ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የፍላጎቱን 30 በመቶ የሚሸፍንና በኣመት 37 ሺ ቶን ፖሊኦቲን ማምረት የሚችል ፋብሪካ
በዕቅድ የተያዘ ሲሆን ይህም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሊሳካ እንዳልቻለ ሰነዱ ይጠቁማል፡፡
ለጎማ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን 3ሺ ካሬሜትር የጎማ ዛፍ ለመትከል 6ሺ700 ቶን የሚያመርት የራበር ፕሮሰሲንግ ፕላንት ለማቋቋም በዕቅድ ቢያዝም የጎማ ዛፍ ልማት ከማከናወን በስተቀር የፋብሪካውን ግንባታ ማከናወን አልተቻለም፡፡
በዓመት 35ሺ ቶን ሶዳ አሽ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ለመገንባት ከግል ባለሃብቶች ጋር ስራው ቢጀመርም እስካሁን ስራው መጠናቀቅ የቻለው 40 በመቶ ገደማ ሲሆን እስከዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ መጠናቀቅ እንደማይችል ታውቆአል፡፡
የ300ሺ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት በዕቅድ የተያዘ ሲሆን እስካሁን ፕሮጀክቱ ከ30 በመቶ በላይ መራመድ አልቻለም፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካው ለመጓተቱ አንዱና ዋናው ምክንያት በመከላከያ የሚመራው የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማሽነሪ እንዲፈበርክ በመታሰቡና ይህ ሊሳካ ባለመቻሉ ነው፡፡
በዘርፉ ኤክስፖርትን ለማሳደግ በእቅድ ዘመኑ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የታቀደ ቢሆንም የተሳካው 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወይንም የእቅዱን 55 በመቶ ብቻ መሆኑ የአፈጻጸሙን ዝቅተኛነት ያሳያል፡፡ በያዝነው 2007 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት
505 ሚሊየን አሜሪካን ዶላር ከኤክስፖርት ለማስገባት ታቅዶ 38 በመቶ መፈጸም መቻሉ ዘርፉ አደጋ ላይ መሆኑን እንደሚሳይ ሰነዱ ይጠቁማል፡፡
መንግስት የያዘው የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ እጅግ የተለጠጠና የማይፈጸም በመሆኑ እንዲከለስ በተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለያዩ ምሁራን የቀረቡትን ገንቢ ሃሳቦች ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ባለመቀበሉ የሀገር ሀብት ብክነትን ያስከተለ ኪሳራውን ለመቀበል እየተገደደ ነው፡፡