አይ ኤስ በ30 ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ በመላው አለም እየተወገዘ ነው

ሚያዝያ ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያውያን ሳምንቱን በሀዘን ተውጠው አሳልፈዋል። በየመን የተጀመረው የኢትዮጵያውያን የድረሱልኝ ጩኸት በደቡብ አፍሪካ እና በሊቢያ ተሰምቷል።

30 ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ በአይ ኤስ ወታደሮች የተገደሉበት ዜና መላውን አለም እያነጋገረ ነው። ኢትዮጵያውያን ሀዘናቸውን ከመግለጽ በተጨማሪ ምን እናድርግ እያሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው። በፌስቡክ እና በማህበራዊ ድረገጾች የፖለቲካ እምነታቸውም ሆነ ሃይማኖታዊ ጎራ ሳይለያቸው በአንድነት ሀዘናቸውን የሚገልጹ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጨምሮአል።

እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን የኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን ማንነት እያጣራሁ ነው በማለት መግለጫ መስጠቱ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ሳይቀር በመንግስታቸው አንገታቸውን መድፋታቸውን ገልጸዋል። ግፊቱ ከአያቅጣቸው መምጣቱን የተገነዘበው መንግስት በማግስቱ ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። የሶስት ቀናት ሀዘንም እንደሚታወጅ ተናግሯል። ፓርላማው ስለሚወሰደው እርምጃ እንደሚነጋገር ገልጿል። የመንግስትን መግለጫ ተከትሎ አዲስ አበባ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣው ተመሳሳይ መግለጫ፣ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ሳይቀር ውግዘት አስከትሎአል። መግለጫው የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን ብሎአል።

የቤተክርስቲያን መግለጫ ያሳዘነው ታዋቂው ጸሃፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  “በምንም ለማናውቃቸውና ለማያውቁን የኢንዶኔዥያ ዜጎች ሱናሚ መታቸው ብለን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ያደረግን ሰዎች ለሚያውቁንና ለምናውቃቸው ክርስቲያን ወገኖች

ጸሎት ለማድረግ ለምን እንደከበደን፣ ‹ማንነታቸው ተረድተን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት አስፈላጊውን እናድርጋለን› የሚለው መግለጫ ” ለመሆኑ ከክርስትና በላይ ምን ማንነት አለ? የብሔር፣ የብሔረሰብ ማንነት ነው የምታጣሩት? ከዚያ ይልቅ ሁኔታውን

የሚከታተል፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኝና ለቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊም ቀኖናዊም ተግባር ነገሮችን የሚያመቻች ሲኖዶሳዊ ኮሚቴ ይቋቋማል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ምነው በአንድ አጥቢያ ገንዘብ ተወሰደ ሲባል ሲኖዶሳዊ ኮሚቴ ይቋቋም የለምን?” ሲል ጠይቋል።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ድርጊቱን አጥብቀው አውግዘዋል። ሰማያዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ በየመንና ደቡብ አፍሪካ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ሰቆቃና ግፍ ሀዘናችን ሳይበርድ አረመኔው የአይ ኤስ አይ ኤስ (ISIS)

ቡድን 30 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን በጭካኔ ስለማረዱና ስለመግደሉ በብዙሀን መገናኛ መዘገቡ ሀዘኑን እንዳከበደው ገልጿል።“ይህ ሀገር ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር እና የመልካም አስተዳደር እጦት ለማምለጥ በስደት ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊና የጭካኔ እርምጃ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ልብ ሰብሯል፡፡”የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ፤  “ከምንም በላይ አሁንም የእነዚህን ዜጎች ጉዳይ በአግባቡ የሚይዝ መንግስት እንደሌለን መታወቁ የኢትዮጵያውያንን ሀዘን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡”ብሏል።

“በሌላ በኩል ራሱ ገዳዩ ቡድን ኢትዮጵያውያንን እንደገደለ  በገለጸበት፣ በተለያዩ ሚዲያዎችና አይ ኤስ አይ ኤስ በለቀቀው ቪዲዮም የተገደሉት መልክና የፊት ገጽታ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሆኖ ሳለ፣ የውጪ መንግስታት በኢትዮጵያውያን ላይ

የተፈጸመውን ጭካኔ እያወገዙ በሚገኙበት ወቅት እና፣ ከምንም በላይ ደግሞ ከዚህ ውጭ የሟቾቹን አስከሬን አግኝቶ ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹  ሰለባዎቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ግብፅ የሚገኘው ኢምባሲ አላረጋገጠም›› በማለት

የሰጠው መግለጫ ሀዘናችንን በእጅጉ አብዝቶታል፡፡” ብሏል ሰማያዊ ፓርቲ።

ፓርቲው አያይዞም፦”እንደ ሀገር አፍረናል፡፡ በተለመደው መልኩ አንድ መንግስት ነኝ የሚል አካል ሊያደርግ ይገባው የነበረውን ሚና ባለመወጣቱም ብዙዎቹን አስቆጥቷል፡፡”ብሏል።መንግስት በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በጥብቅ

እንዲወጣ ፓርቲው አሳስቧል።

አርበኞች ግንቦት7 በበኩሉ “አይ ኤስ በጥንት በጭለማ ዘመን እንኳን ባልነበረ ጭካኔ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎችን በማረድ የሚደሰት፤ በሰው ዘር ሁሉ ላይ የመጣ አውሬ መሆኑን ነብዩ መሐመድ አትድረሱባቸው ያሏቸውንም ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በማረድ አረጋገጧል። ይህ አሰቃቂ ተግባር ምንም ዓይነት አመክኖ ሊቀርብለት የማይችል አረመኔዓዊ የሽብር ጥቃት ነው”  ብሎአታል።

አርበኞች ግንቦት 7 “ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አይ ሲስን በጥብቅ እንዲያወግዙ፤ በአመቻቸው መንገዶች ሁሉ እንዲታገሉት ” ጥሪ አቅርቧል።

የአይ ኤስን የሽብር ተግባራት ከእስልምና እምነት ጋር ማያያዝ ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ፤ ብዙሃን ሙስሊሞች የአይ ኤስና መሰል ቡድኖችን አካሄድ የሚቃመው መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 ገልጿል። ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር ተዋደውና

ተፋቅረው የኖሩና እየኖሩ ያሉ ሲሆን የሁለቱ ሀይማኖቶች ተከታዮች ተደጋግፎ መኖር ለሀገራችን ህልውና ወሳኝ  ጉዳይ መሆኑም አስታውሷል።

“በደቡብ አፍሪቃ ወገኖታችን ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል፤ በስለት ተዘልዝለዋል፤ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፤  700 ዜጎች የሜዲትራኒያን ባህር በጀልባዎች ሲሻገሩ መስመጣቸው ተሰምቷል። በየመን ደግሞ በርካታ ወገኖታችን በጦርነት እሳት ውስጥ

እየተማገዱ ናቸው” ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ ኢትዮጵያዊያን በአገራችን የሰፈነውን የነፃነት እጦት፣ የፍትህ መጓደልና የኑሮ መክበድ ሸሽተን በሄድነት አገር ሁሉ የሚጠብቀን አሰቃቂ ሞትና ውርደት  በህወሓት አገዛዝ ብሉሽነት በመሆኑ ይህንን ብልሹ አገዛዝ አስወግደን

በምንወዳት አገራችን ተከብረን መኖር እንችላለን ብሎአል።   አርበኖች ግንቦት 7 የኢትዮጵያዊያን መከራ እንዲያበቃ ስደት ይብቃ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ ቤልጂየም የሚገኘው የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ህብረት ፣ ሌብማ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ አውግዟል።

ሊብማ ድርጊቱ የእስልምናን መርሆዎችና ትምህርቶች የሚጻረር ነው ብሎአል። እስልምና ለሰው ልጆች ህይወት ትልቅ ከበሬታ እንዳለው የሚገልጸው ሊብማ፣ የአንድ ንጹህ ሰው ህይወት መጥፋት የአካባቢው ሰው ህይወት መጥፋት እንዲሁም የአንድ ሰው ህይወት ማደን የአካባቢውን ሰው ህይወት ማዳን አድርጎ ይመለከተዋል ብሎአል።

በአይ ኤስ የተፈጸመው ድርጊት ከሞራል፣ ከሃይማኖት እና ከፖለቲካ አንጻር ምንም ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው ሲል በመግለጫው አክሏል።

በኢትዮጵያ በእስልምናና በክርስትና መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት አንጸባራቂ ነው የሚለው ሌብማ፣ በነብዩ ሙሃመድ እና በክርስያኑ ንጉስ መካከል የነበረው ግንኙነት አንዱ የሌላውን ሃይማኖት በጠላትነት ማየት እንደሌለበት የሚየሳይ ነው ብሎአል። በተለያዩ ጊዜያት

በፖለቲካ ስርአቱና በሃይማኖቶች መካከል ችግሮች ተከስተው የነበረ ቢሆንም፣ በክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል አንድነት ሰፍኖ መቆየቱን፣ አሁንም አይ ኤስን የመሳሰሉ ቡድኖች የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች የሙስሊሞች ጠላቶች እንደሆኑ  አድርገው ሊከፋፍሉን

የሚሞክሩትን በጋራ እንቋቋማቸዋለን ብሎአል።

ሊብማ በደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን ግድያም በጽኑ አውግዟል። በተለይ ኢትዮጵያውያን ኢላማ ሆነው በቁማቸው መቃጠላቸው እጅግ እንዳሳዘነው የቤልጂየም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድርጅት አስታውቋል።

ለብማ ኢትዮጵአውያንን ለስደት እየዳረገ ያለው የተበላሸው የኢህአዴግ ፖሊሲ መሆኑን ገልጿል። የሰብአዊ መብት ተማጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች  መታሰራቸውን የገለጸው ልብማን፣ ለዚህ ሁሉ ስቃይ ኢህአዴግ ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብሎአል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የነጻነት እጦት መቅረፍ ካልተቻለ፣ በሊቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የታየው ችግር እንደማይቆም አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግስትም ድርጊቱን በጥብቅ አውግዟል። የአሜሪካ መንግስት ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመንቶ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን እንደሚቆም ገልጿል። በሊቢያ ያለው ችግር የፖለቲካ መፍትሄ እንደሚያሻው አይ ኤስ የፈጸመው ድርጊት ያሳያል ሲል

መግለጫው አትቷል።

በሌላ ዜና ደግሞ በአይ ኤስ በግፍ ከተገደሉት መካከል ሁለቱ በጨርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 25 ይኖሩ የነበሩ ወጣቶች መሆናቸውን የአካባቢው ተወላጅ የሆነው ዳንኤል ፈይሳ ተናግሯል። ዳንኤል ወጣቶቹ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተወዳጆች እንደነበሩ ተናግሯል።

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑን እየገለጹ ነው። ቤንጋዚ ውስጥ በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እንዳለው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ከአምና ጀምሮ በአክራሪው ሃይል ተይዘዋል።