“ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል”ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ገለጸ።

ሚያዝያ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው ፦«ከራሳችን ውጪ ለችግራችን ደራሽ መንግስት የለንም!»በሚል ርእስ በየመንና በደቡብ አፍሪካ በሚገኚ ኢትዮጵያውያን ላይ

እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ፣የኢትዮጵያውያን የውርደት ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሰሞኑን ከተከሰተው እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ አድርሶናል

ብሏል።

“የመን ውስጥ በተከሰተው ጦርነት ተጎጂ የሆኑትን የውጭ ዜጎች መንግስታቶቻቸው ቀድመው ሲያስወጡ ለኢትዮጵያውያን ግን የሚደርስላቸው አልተገኘም”ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ይህንን

ውርደትም ወገኖቻችን «የመን ውስጥ የቀረነው እኛና ውሻ ብቻ ነን» ሲሉ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ እንደገለጹት አውስቷል።

“ ኢትዮጵያውያን ላይ የመድፍ፣ የሞርታርና የአውሮፕላን ድብደባ ሲዘንብባቸው በመከራ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስልክ እንዲደውሉ በፌስቡክ ላይ በመለጠፍ ከማላገጥ ውጭ ምንም

ያላደረገው የህዝብን ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው ገዥው ፓርቲ ፤ ይባስ ብሎ ለራሱ ስልጣን ይጠቅሙኛል ያላቸውን የጦርነቱን ተሳታፊዎች ደግፎ መግለጫ መስጠቱ- የኢትዮጵያውያንን

ስቃይ እጥፍ ድርብ አድርጎታል”ብሏል።

በአጭሩ ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ በማያገባውና በማይወጣው ዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ ሀገራችንን ሲዘፍቅ ፤ ጦርነቱን ያወጀው፦ የሚደርስላቸው ባጡ ምስኪን ኢትዮጵያውያንና

በኢትዮጵያ ላይ ነው ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲ።

በየመን የተከሰተውን መርዶ ሰምተን ሳንውል ሳናድር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አስደንጋጭ አደጋና እና ሰቆቃ ልንሰማ ተገደናል የሚለው የፓርቲው መግለጫ፤ኢትዮጵያውያን

ሀብትና ንብረታቸው መዘረፉ ሳያንስ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታትለናል ብሏል።

የዚህ አሰቃቂ አደጋ ሰለባ የሆኑ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በቶሎ ከደቡብ አፍሪካ ሲወጡ፣ እንዲሁም ሀገራቱ ዜጎቻቸውን መታደግ ያስችላል ያሉትን መፍትሄዎች ሲያስቀምጡ እና ሲያስጠነቅቁ ቢደመጥም፤

ኢህአዴግ ግን እንደተለመደው የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃና ስቃይ ከምንም እንዳልቆጠረው በግልፅ እየታየ ነው ሲልም ሰማያዊ ፓርቲ ቁጣውን ገልጿል።

በእርግጥ ላለፉት 24 ዓመታት ኢህአዴግ ሀገር ውስጥ የሚኖሩትን ዜጎች ሲያሰቃይ፣ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንም የሆነ ያልሆነ ስም እየለጠፈ በጠላትነት ሲፈርጃቸው እንደቆየ አይተናል

ያለው ፓርቲው፤ ኢህ አደግ  ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የራሱን የግል ጥቅም ሲያሳድድም መቆየቱን አውስቷል።

በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ባሉት ተደጋጋሚ ግፎች ተሸፈነ እንጅ ሰሞኑን ሌላ ኢህአዴግ ለዜጎች እንደማይጨነቅ የታየበት ክስተት እየተፈፀመ ያወሳው ሰማያዊ ፓርቲ፤  ኢህአዴግ ለሱዳን መንግስት

አሳልፎ በሰጠው ሰፊና ለም የሀገራችን ሉዓላዊ መሬት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ሌላ አሳፋሪ እና አሰቃቂ ወንጀል እንደተፈፀመ ምመዘገቡን ጠቅሷል።

“ኢትዮጵያውያን የሀገራችንና የራሳችን ክብር እና ደህንነት ማስጠበቅ ካለብን መጀመሪያ ሀገራችን ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፅኑ መታገል የግድ ይለናል።”ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ አስተዳደር፣

ዴሞክራሲያዊና ለዜጎች የሚያስብ ስርዓት ቢኖር መጀመሪያውኑም ወገኖቻችን በገፍ ለአደጋ ወደሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ባልተሰደዱ ነበር።”ብሏል።

በመሆኑም በቅድሚያ ክብራችንን ለማስመለስ የነፃነት ትግሉን አጠናክረን መቀጠል አልብን ብሏል-ፓርቲው።

ሰማያዊ ፓርቲ አክሎም፦“ክብራችንን ልናስመልስ የምንችለው ሀገራችን ውስጥ እንዳንኖር ያደረገንን ስርዓት ቀይረን አንድም በገዛ አገራችን መኖር ስንችል፣ አንድም በአደጋ ወቅት ሊደርስልን የሚችል ተቆርቋሪና

ለዜጎች የሚያስብ መንግስት መመስረት ስንችል ብቻ መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል።”ብሏል።