ሚያዝያ ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በገጠር ያሉ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ቤተሰቦች ያለባቸውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ በሴፍቲኔት እንዲታቀፉ የተደረገ ሲሆን ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥበ 9 ቢሊየን ብር ለክልሎች ተላልፎ፣ ከዚህ ውስጥ ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ለተጠቃሚዎች መከፈሉን መረጃው ያሳያል፡፡ በተጠቀሰው ወራት ወደወረዳዎቹ ከ32 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ እህል ተጓጉዞ መከፋፈሉም ታውቆአል፡፡
የቀጣይ ዘመን የሴፍቲኔትና ቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራሞች የሚረዳ የ 600 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ከዓለም ባንክ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከ23 ዓመታት የስልጣን ቆይታ በሃላ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን አረጋግጫለሁ ቢልም አሁንም በገጠርም በከተማም የሚራቡ እና ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ በሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚረዱ ከ7 ሚሊየን በላይ ወገኖች የሚገኙ መሆኑ ታውቋል፡፡
የዋጋ ንረትን ለመከላከል በሚል ስም በከተሞች ለሚኖር ሕዝብ በመቶ ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ ስንዴ ከውጪ ሀገር እየሸመተ በማስገባት እያከፋፈለ መሆኑ በምግብ ሰብል ራሳችንን ችለናል የሚለው ዜና ተራ ፕሮፖጋንዳ እንዳደረገው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እየተጠናቀቀ ባለው የኢህአዴግ አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሃግብር ግብርናውን ወደኢንዱስትሪ አሸጋግሮ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ቢያልምም ፣ ዘርፉ ባለበትም ለመቀጠል ሳይችል በመቅረቱ ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለፉት አራት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ 14 ነጥብ 9 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ የነበረ ቢሆንም ዘርፉ በተጨባጭ ማደግ የቻለው ግን 7 ነጥብ 2 በመቶ ነው፡፡
በነዚህ ዓመታት በተለይ በግብርናው ዘርፍ እንዲሁም የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል፣ ሀገሪቱ አቅዳው የነበረውን ተከታታይና ፈጣን የሆነ ዕድገት የማስመዝገብ ዕቅድ ማሳካት ባለመቻሉ የጠቅላላ ኢኮኖሚ መናጋትን ማስከተሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡