መጋቢት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሱዳን ትሪቢውን የግንባሩን ሊቀመንበር ተዋት ፖል ቻይን ጠቅሶ እንደዘገበው ፣ የደቡብ ሱዳን አማጽያን፣ የሳልቫኪር መንግስት ለኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ግንባር ወታደራዊ ስልጠና፣ የገንዘብ እንዲሁም
የሎጅስቲክ ድጋፍ ያገኛል በሚል ያቀረበው ወቀሳ ተቀባይነት የሌለው ነው።
አማጽያኑ የፖል ቻይ ጦር ወደ ጋምቤላ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም አስቧል በማለት ክስ አሰምተው ነበር። ፖል ቻይ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንደማይገቡ ገልጸው፣ በሱዳን መንግስት ተቃዋሚዎች የቀረበው ክስ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ በሚገኙ
የኑዌር አባላት ዘንድ እርሳቸውንና ድርጅታቸውን ለማስጠላት ነው ብለዋል። የማቻር ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማግኘት ሲል የለቀቀው ዜና ነው ሲሉም በእርሳቸውና በድርጅታቸው ላይ የቀረበውን ውንጀላ አስተባብለዋል።
ፖል ቻይ ሟቹ ጆንጋራንግ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጭ ድርጅትን ሲመሰርቱ እርሳቸው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረጉ ገልጸው፣ እርሳቸው እገዛ አድርገው ባቋቋሙት ድርጅት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እንደማይፈልጉ አክለዋል።
ፖል ቻይ በደርግ ጊዜ የጋምቤላ ክልል ገዢ እንዲሁም የጸጥታ ጉዳይ ሃለፊ ነበሩ። ከቀድሞው መሪ መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ቻይ፣ የኢህአዴግን መንግስት በትጥቅ ትግል ለመጣል በመታገል ላይ ናቸው።
ፖል ቻይ በዘር ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥልና አገሪቱን የሚከፋፍል ነው በማለት አጥብቀው ይቃወሙታል። እርሳቸውም ሆነ ድርጅታቸው የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ሲሉ በመታገል ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።