መጋቢት ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በሚል ክልሎችን ህወሃት፣ ብአዴንና ኦህዴድ እንዲያስተዳድሩዋቸው ካከፋፈለ በሁዋላ፣ የክልሎችን የመጀመሪያ ሪፖርት ሰሞኑን ተቀብሎአል፡
ኢሳት ቀደም ብሎ በሰራው ዘገባ የሶማሊ ክልል በህወሃት፣ ሃረሪ በኦህዴድና ህወሃት፣ አፋር በህወሃት፣ ቤንሻንጉል በብአዴን እንዲሁም ጋምቤላ በህወሃት እንዲተዳደሩ መወሰኑን ዘግቦ ነበር።
እነዚህ አዳጊ የተባሉ ክልሎች ማንኛውንም የስራ እንቅስቃሴያቸውንና እቅዶቻቸውን ለእነዚህ ድርጅቶች የማቅርብ ግዴታ ተጥሎባቸው የቆየ ሲሆን፣ ዋና ዋና ድርጅቶች ደግሞ እቅዶችን ከማጽደቅ በተጨማሪ ፣ ክልሎቹ ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት
አስተያየቶቻቸውን ይሰጣሉ። እነዚህ ድርጅቶች የአናሳ ክልሎችን ካቢኔዎች እስከመገምገም የሚደርስ ስልጣንም አላቸው።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰሞኑን ባቀረበው ሪፖርት ብአዴን ለክልሉ እያደረገ ያለውን እገዛ አድንቋል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 32 ሺ የኢህአዴግ ደጋፊ አባላት እንዳሉ ተደርጎ በክልሉ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ ብአዴንን በመወከል ለሪፖርቱ አስተያየት
የሰጡት አቶ አዲሱ ለገሰ ፣ የኢህአዴግ ደጋፊ አባላት ቁጥር በክልሉ ከተመዘገበው መራጭ ጋር አብሮ ስለማይሄድ ተስተካክሎ ይቀረብ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።