የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር -የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችን ወቀሱ

መጋቢት ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  ‹‹ኢህአዴግ እያታለላችሁ ነው፡፡ እናንተም ለመታለል ዝግጁ ሆናችኋል›› ሲሉ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለአውሮፓ ህብረት መልእከት አስተላለፉ።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር  ይህን ያሉት የአውሮፓ ህብረት ዛሬ መጋቢት 1/2007 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ጽ/ቤቱ ባደረገው ስብሰባ  ላይ ነው።

 ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ ያላቸው 20 ያህል የህብረቱ አባል አገራት  አምባሳደሮችና ተወካዮች በተገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ በተጋባዥ እንግድነት የተገኙት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ከህብረቱ ተወካዮች ጋር በወቅቱ ሀገራዊ  ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውነ የነገረ-ኢትዮጰያ ዘገባ ያመለክታል።

የሀገራቱ ተወካዮች  በወቅታዊው የምርጫ ሂደት ፣ በሰማያዊ ፓርቲ  የምርጫ እንቅስቃሴ፣ በምርጫው ሂደት እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች፣ በፓርቲው አማራጭ ፖሊሲዎች፣ በድርጅቱ ጥንካሬ፣ የአንድነት አባላት ወደሰማያዊ መምጣታቸው ለትግሉ በሚኖረው ትርጉምና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጥያቄዎችን ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በሰጡት ምላሽ ሰማያዊ ፓርቲ ከ200 በላይ ዕጩዎች በህገ ወጥ መንገድ እንደተሰረዙበት፣ የፓርቲው የቅስቀሳ መልዕክት ከ6 ጊዜ በላይ በሚዲያ እንዳይተላለፍ መከልከሉን፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ድብደባ፣ እስራትና ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ  በመጥቀስ፤ በምርጫው ሂደት ኢህአዴግ አፋኝነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸው ትግሉን እንደሚያጠናክረውም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከሰማያዊ በተጨማሪ በአንድነትና መኢአድ  ፓርቲዎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ህገ ወጥ  መሆኑን  የተናገሩት ሊቀመንበሩ፤ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በኃይል እያጠፋ ‹‹ከእኔ ውጭ አማራጭ የለም›› የሚል አቋሙን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳየት እንደሚፈልግ ለህብረቱ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነር ይልቃል በዚሁ ማብራሪያቸው‹‹የአውሮፓ ህብረት ችግር የኢትዮጵያን ችግር በአውሮፓውያን ተቋማትና የስነ ልቦና ልክ ማየቱ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። የአውሮፓ ህብረት ‹‹የተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲያቸው ምንድን ነው?›› በሚል የሚያነሱትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ያወሱት የሰማያዊ ሊቀመንበር፤ መደረጀትና መናገር ያልቻለውን የኢትዮጵያን ህዝብ በአውሮፓ ተቋም አይን አይቶ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ማንሳት፤ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ብዙም እርባና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ይልቃል አያይዘውም፦ ‹‹በእኛ አገር የፖለሲ አማራጭ ለማቅረብ አይቻልም፡፡ ሚዲያው በገዥው ፓርቲ የተያዘና የተቃዋሚዎችን ሀሳብ የማያስተናግድ ዝግ ሆኗል፡፡ እናንተ እንደምትገምቱት የፖሊሲ አማራጭ ለማቅረብ አመች ሁኔታዎች ቢኖሩ፤ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ የተሻለ ምሁራንና ሀሳብ ስላላቸው- ዝርዝር ፖሊሲያቸውን ለማቅረብ አይቸገሩም ነበር፡፡››ብለዋል።

ኢህአዴግ፦ ‹‹ተቃዋሚዎች የተበታተኑና የተዳከሙ በመሆናቸው ለቀጠናው ሰላም አማራጩ እኔ ብቻ ነኝ›› ብሎ የአውሮፓ ህብረትን እንደሚያታልል የገለጹት ኢ/ር ይልቃል፤ ‹‹ እናንተም-ኢትዮጵያውያን ካላቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ማየት ስላልቻላችሁ፤ ኢህአዴግ እያታለላችሁ ነው፡፡ እናንተም ለመታለል ዝግጁ ሆናችኋል፡፡›› ሲሉ የአውሮፓ ህብረትን ወቅሰዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለ6ኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ መከልከሉ ታውቋል።