<<ችሎት ደፍራችሁዋል ተብለው ፍርድ የተላለፈባቸው እነ አብርሀ ደስታ፦<<የደፈርነው አሻንጉሊት እና  ወትሮም የተደፈረ  ችሎት ነው>>ሲሉ ተቃውሟቸውን ገለጹ።

መጋቢት ፩(አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ ፓርቲ  አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው  የሰባት ወር እስራት ተፈረደባቸው።

የልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት  ዛሬ መጋቢት 1 ቀን  2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት  በመድፈር በሰባት ወር እስራት እንዲቀጡ የወሰነባቸው አብርሀ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋና ዳንኤል ሺበሺ ናቸው። የካቲት 26/2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት የነበረውን  አቤቱታ  ፍርድ ቤቱ  ውድቅ ማድረጉን  ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡ፣ 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ  ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት የአቶ የሺዋስን ጭብጨባ  ደግፈው በመናገራቸው  ነበር ችሎት ደፍረዋል ተብለው የተከሰሱት።

በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ በእያንዳንዳቸው ላይ   የሰባት ወራት እስራት ወስኗል፡፡ የቅጣት ውሳኔው እንደተነበበ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም በድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ተከሳሾቹ  በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ  የተባሉ ሲሆን፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሌላ የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በችሎቱ ሦስቱ ተከሳሾች፦ ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡ ፍርድ ቤቱ-ተከሳሾቹን  አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው፤ ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአረናው አመራር አብርሀ  ፦‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ወትሮም የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል  ተናግሯል፡፡

በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፦ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል  በጥያቄ መልክ ምላሹን ሰጥቷል። አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ
ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡
አቶ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና  ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና
እንረዳለን፡፡›› ሲል  ተናግሯል፡፡ በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ በመምጣቱ  ዳኞቹ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ  ማሳወቁን ተከትሎ  ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡