የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በሆኑ የጋምቤላ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እንደሚገደሉና የጸጥታው ሁኔታ እየተበላሸ መሆኑን በተለያዩ የመንግስትና የግል ስራዎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ገልጸዋል።
መታሃር፣ ላሬ፣ ኢታንግ እንዲሁም ፑጊዶ በሚባሉ አካባቢዎች ማንነታቸው በውል የማይታወቁ ታጣቂዎች አብዛኛውን ጊዜ በግል ኩባንያዎች ተቀጥረው በሚሰሩ ዜጎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው። እነዚህ ታጣቂ ሃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስና ልዩ ሃይል አባላትም በንጹሃን ዜጎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የካቲት 13 ቀን ማቲያስ ዘነበ የተባለው የታያም ኢንጂነሪንግ ኩባንያ አማካሪ ተገድሎ አስከሬኑ ወደ ደብረዘይት ተሸኝቷል። በሌሎች አካባቢዎችም እንዲሁ በየጊዜው ሰራተኞች እየተገደሉ አስከሬናቸው ወደ መሃል አገር እንደሚሸኝ ይናገራሉ።
በአካባቢው የሚታየውን የመሬት መቀራመት በመቃወም የአካባቢው ተወላጆች በተቀጣሪ ሰራተኞች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል የሚሉት ነዋሪዎች፣ መንግስት በቂ የሆነ እልባት ማስገኘት እንዳልቻለም ያክላሉ።
በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በጋምቤላ ከውጭ አገር ባለሃብቶች ቀጥሎ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የያዙት የህወሃት ባለስልጣናት ናቸው። በተለይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አባይ ጸሃየ ዘመዶች እጅግ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እንደያዙ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። ወ/ሮ አዜብ በተር ፍላይ አግሮ እንዱስትሪ (butterfly Agro Industry) በተበለ ኩባንያቸው ሰፊ መሬት ይዘው ቢቀመጡም፣ ቦታውን እስካሁን አላለሙትም። እንደነዚህ ሰዎች አገላለጽ፣ የባለስልጣኖቹ ዘመዶች ሰፋፊ ቦታዎችን ከክልሉ ባለስልጣናት ይረከቡና ከባንክ ብድር ይወስዱበታል፣ በተበደሩት ብድር ግን የእርሻ ቦታውን ከማልማት ይልቅ፣ ሌሎች ስራዎችን ይሰሩበታል።
የጋምቤላ መሬት ከህወሃት ባለስልጣናት በተጨማሪ፣ ቀድሞ የህወሃት የጦር መኮንኖች በነበሩ ሰዎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝም ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።