የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት እየተባለ እስከ አስር ደረጃ ድረስ የስራ ተቋራጭነት ፈቃድ የሚሰጥ ሲሆን ይህንን ፈቃድ ለማግኘት እንደዶዘር፣ ግሬደር፣ እስካቭተርና ፒክ አፕ ያሉ መኪኖችን መያዝ በቅድመ ሁኔታነት የሚጠየቁ ቢሆንም፣ ሥራ ተቋራጮች እነዚህ ተሸከርካሪዎች እንዳሉዋቸው በማስመሰል ከትራንስፖርት ባለስልጣን አንዳንድ ሃላፊዎች ጋር እየተሻረኩና የጥቅም ትስስር እየፈጠሩ ሐሰተኛ ሊብሬ በማቅረብ ፈቃዱን የሚወስዱ መሆኑ ታውቆአል፡፡
ፈቃዱ ከወሰዱም በሃላ የመንገድና የሕንጻ ፕሮጀክቶችን በማያዋጣ ገንዘብ ጨረታ ተሳትፈው በማሸነፍ ቅድሚያ ክፍያ ይዘው የሚሰወሩበትና ደረጃውን ያልጠበቀ ግንባታ የሚያካሒዱበት ሁኔታ በብዛት እየተከሰተ መሆኑ ጥናቱ አሳይቶአል፡፡
በሀገሪቱ ከፍተኛ ሙስና ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች ቀዳሚው የግንባታ ዘርፉ ሲሆን ይህ ሙስና ሊስፋፋ የቻለውም መንግስት የሀገር ውስጥ ስራ ተቋራጮችን ለማበረታታት በሚል በርካታ ፕሮጀክቶችን በቀላሉ ስለሚሰጥና በዚህም ሒደት ሙያው የሌላቸው ሰዎች ወደዘርፉ ገብተው አለአግባብ ለመጠቀም በሚያደርጉት ያልተገባ ውድድር በማየሉ ምክንያት ነው ተብሎአል፡፡
በዘርፉ በተለይ የፈቃድ አወጣጥ ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋበት ሲሆን ተሸከርካሪ ሳይኖር የተሽከርካሪ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ ስለሚታደል ሰዎቹ በቀላሉ ፈቃድ አግኝተው በአንድ ጊዜ በመቶ ሚሊየን ብሮች የሚገመቱ ፕሮጀክቶችን የሚያገኙበት አሰራር በመስፈኑ የህዝብ ሐብት በቀላሉ እየተዘረፈ መሆኑን ጥናቱ አሳይቶአል፡፡
ፖሊስ በዚህ የሙስና ተግባር የተጠረጠሩ አንዳንድ የስራ ተቋራጮችን ለመያዝ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ብዙዎቹ የሙስና ስንሰለታቸው እስከከፍተኛ ባለስልጣናት የተዘረጋ በመሆኑ ዋናዎቹን ተጠርጣሪዎች እስካሁን መያዝ አለመቻሉ ታውቆአል፡፡
በሀገሪቱ እንደመንገድ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመቶ ሚሊየን ብሮች ቢፈስባቸውም ግንባታዎቹ የተመረቁበትን አንደኛ ኣመት ሳያከብሩ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑበት ሁኔታ በብዛት እየተከሰተ ነው፡፡