ግብጽ ኢትዮጵያና ሱዳን በአባይ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ

የካቲት ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካርቱም ሱዳን ውስጥ ሲደረግ የነበረው ሶስቱ አገራት ድርድር በስኬት መጠናቀቁን የሶስቱም አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስታውቀዋል። የግብጽ የውሃ ሃብት ሚኒስትር  ስምምነቱ ግብጽ በግድቡ ላይ ያላትን ስጋት

ያስወገደ ነው ብለዋል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ካርቲ በሶስቱ አገራት መካከል ሙሉ ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል። የተስማሙባቸውን መርሆዎች ለሶስቱን አገራት መሪዎች በማቅረብ እንዲጸድቁ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ስምምነቱ በሶስቱ አገሮች መካከል አዲስ የግንኙነት መንገድ የሚፈጥር ነው።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሻኩሪ ደግሞ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው መርሆዎች፣ በሶስቱ አገራት መካከል አዲስ ትብብር ለመጀመሩ አመላካች ነው ብላል። ሶስቱም መንግስታት ስምምነቱን ቢያወድሱትም ዝርዝሩን ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም። ይሁን እንጅ

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ግድቡን በተመለከተ ተጨማሪ አጥኚ ቡድን አያስፍልግም በሚል ይዛው የነበረውን አቋሟን መቀየሩዋንና ግብጾች አለማቀፍ አጥኚ ይቋቋም እያሉ ሲወተውቱ የነበረውን መቀበሏን አለማቀፍ አጥኚዎችን ለመምረጥ ከተደረገው ጫረታ ለመረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያ ቀደም ብላ የያዘችውን አቋም ለመለወጥ ለምን እንዳስፈለጋት ግልጽ አላደረገችም። ይሁን እንጅ ግብጽ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ላይ የምታሳድረውን ተጽእኖ በመፍራት፣ ከግብጽ ጋር ለመወዳጀት በማሰብ ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

አጥኚ ቡድኑ ስራውን ሲጨርስ የሚያቀርበው ሀሳብ ወሳኝ ሲሆን፣ ቡድኑ ግድቡ በግብጽ ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ያስከትላል ብሎ ከወሰነ ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግንባታ ሂደት ላታከናውን ትችላለች።