ሶስት ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጭ የወጣበት ድልድይ የጥራት ችግር አለበት ተባለ

የካቲት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአባይ  ወንዝ ላይ የተሰራዉ 108 ሜትር ርዝመት እና አንድ ነጥብ ስድስት  ሜትር ስፋት ያለው ተንጠልጣይ ድልድይ  በሃገሪቱ ብቸኛዉ የተንጠልጣይ  ድልድይ በመስራት በሚታወቀው  ሄልቬታስ ሲዊዝ ኢንተርኮኦፕሬሽን በተሰኘ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ በይፋ ተመርቆ ስራ ቢጀምርም፣ በምረቃው ስነስርዓት የተገኙ ባለሙያዎች ድልድዩ የጥራት ችግር እንዳለበት መናገራቸው ነዋሪዎችንና በቦታው ተገኙ አመራሮችን አስደንግጧል፡፡

በአማራ ክልል ገጠር መንገድ ስራዎች ድርጅት የቁጥጥርና ክትትል ኬዝ ቲም ባለሙያ የሆኑት አቶ ይገርማል ታምር በዝርዝር ያቀረቡት  የጥራት ችግር በምረቃ ስነስርዓቱ ለታደሙ የክልል እና የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ኃለፊዎች፣ ግንባታውን በኃላፊነት የሰራው ባለሙያ እና የአካባቢውን ነዋሪዎችን ያስደነገጠ እንደነበር በምረቃው ስነስርዓት  የተገኙ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡

40 በመቶ በሄልቬታስ ፤60 በመቶዉ ደግሞ ከዓለም ባንክ የግብርና እድገት ፕሮግራም በተገኘ ገንዘብ ወጭዉ የተሸፈነው ይህ ድልድይ ለሃምሳ አመታት እንዲያገለግል ታስቦ የተሰራ ቢሆንም  የተሰራበት የድንጋይ አይነት፣የውሃ አጠጣጡ እና ገመዶችን ወጥሮ የያዘው የግንባታ አካል ስጋት ያለበት መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የዳስራ ማርያም እና የጭስ አባይ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን ደግሞ የደራ ወረዳ የተወሰኑ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮችን የዘመናት ጥያቄን የፈታ ሁኗል የተባለለት ታንኳ በር ተንጠልጣይ ድልድይ  እንዲሰራ ላለፉት ሁለት ዓመታት አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ለሚመለከተዉ አካል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

ሄልቬታስ ስዊዝ ኢንተርኮርፕሬሽን የተባለው የግብረ ሰናይ ድርጅት በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች የሚሰራቸውን ተንጠልጣይ ድልድዮች ስራ በብቸኝነትና  ማንም ተቆጣጣሪ በሌለበት ሁኔታ እንደሚሰራና ማኔጅመንቱም በአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ የተያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።  ድርጅቱ በአምስት ክልሎች ከስልሳ በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮችን እንደሰራ በእለቱ የምረቃ ስነስረአት ላይ ተገልጿል፡፡