የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አባይ ጸሃየ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በሃይል እንደሚተገበር በድብቅ ሲናገሩ መደመጣቸው ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አመጽን የሚጋብዝ ብቻ ሳይሆን ፣ ከዚህ ቀደም የደረሰው ደም መፋሰስ ሳይበቃ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዲኖር የሚጋብዝና የሰው ህይወት እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው ሲል የሰብአዊ መብት ሊጉ ባወጣው መግለቻ ጠቅሷል።
የባለስልጣኑ እብሪት የተሞላበት ንግግር ለውይይት፣ ለምክክር እንዲሁም ለዜጎች ይሁንታ ቦታ የማይሰጥ በመሆኑ አደኛ ነው ሲልም አትቷል።
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ ታጣቂ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ 70 የኦሮሞ ተወላጆች መሞታቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውን ያስታወሰው መግለጫው፣ የህወሃት አገዛዝ ባለፉት 24 አመታት በኦጋዴን፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸማቸው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሆን ተብሎ ታቅዶ የተፈጸሙ ናቸው።
አገዛዙ በሚፈጽመው ድርጊት በዘር ማጥፋትና በሰው ልጆች ላይ በሚፈጸም ወንጀል እንደሚያስጠይቀው የሰብአዊ መብት ሊጉ አክሎ ገልጿል። አቶ አባይ ጸሃየ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በሚቃወሙ ላይ ሁሉ ፣የኦህዴድ ባለስልጣኖችን ጨምሮ ፣የሃይል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ዝተዋል።