የካቲት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በጌዲዮ ዞን በኮቾሬ ወረዳ ጨለለቅቱ ከተማ ሃሙስ የካቲት 12 ቀን 2007 ኣም ከቀኑ 11 ሰአት ላይ በተነሳው ግጭት አንድ ሰው ሲሞት ከ10 በላይ የሆኑ ደግሞ ቆስለው ዲላ ሆስፒታል በመታከም ላይ ናቸው። በከተማዋ ያሉ በርካታ ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎም ተነስቷል። የፌደራልና የዞኑ ፖሊስ ወደ ከተማዋ በማምራት ግጭቱን ማብረዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ፖሊሶቹ አሁንም በከተማዋ በብዛት እንደሚገኙና ውጥረት እንዳለ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ግጭቱ በሁለት ሰዎች መካከል እንደተነሳ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ መልኩን ቀይሮ ” መጤዎች” የተባሉትን ነዋሪዎች ወደ መዝረፍና መደብደብ ማምራቱን ይናገራሉ። በ1998 ኣም ተከስቶ እንደነበረው የወረዳው አስተዳዳሪዎች ሆን ብለው አስነስተውታል የሚሉት ነዋሪዎች፣ ለዚህም በምክንያትነት የሚያቀርቡት ከምርጫው ጋር ተያይዞ በአካባቢው ያሉ ተቃዋሚዎች በስፋት መንቀሳቀሳቸው ነው። ተቃዋሚዎችን ግጭት በማስነሳት ለመክሰስና በህዝቡ ውስጥ ሽብር በመፍጠር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የቀዩሰት ዘዴ ነው በማለት የባለስልጣኖችን ድርጊት ኮንነዋል።
በአካባቢው ባሉ ወረዳዎችም ተመሳሳይ ግጭት ሊነሳ ይችላል በማለት ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።