የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐት) ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት የሚያራምዱ ወገኖች መኖራቸውንና ሕገመንግስቱም በተሟላ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን አቶ ስብሃት ነጋ የቀድሞ የህወሃት ሊቀመንበር እማኝነታቸውን ሰጡ፡፡
አቶ ስብሃት ነጋ የካቲት 9 እና 10/2007 ዓ.ም ከወጣው አዲስዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በህወሃት ውስጥ ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት መኖሩን አምነዋል፡፡ «ፖለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት በመንደራችን አለ፡፡ ቢሮክራሲው የጸዳ አይደለም፡፡ እንግዲህ ፓርቲውን የሚመራው መንግስት ነው፡፡ ተወዳዳሪና ቀና የሆነ ቢሮክራሲ ገና አልተገነባም፡፡ ከላይ እስከታች ሕገመንግስቱ በትክክል እየተተገበረ ነው ወይ የሚለው ጎዶሎ አለበት» ብለዋል፡፡
«የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ወይ» በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ስብሃት የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን አረጋግጠው ችግሩን የምንፈታው ሕዝቡን ይዘን ነው ብለዋል፡፡ አይይዘውም «በአስተማማኙ ጎዳና እየተደረገ ያለው ሩጫ ዘገምተኛና እንከን ያለበት ነው፡፡ እንከን ስል ቢሮክራሲው የተሳለጠ ባለመሆኑና የቀናነት ጉድለት ስላለ ሕዝቡ በሚገባ ደረጃ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ የተዛባ አመለካከትና የተንዛዛ አሠራር ይስተዋላል፡፡ ይህ ክፍተት መቀረፍ አለበት፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ስህተቱን ይፋ የሚያደርግና የሚያርም ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ» ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በ1993 ዓ.ም በልዩነት ህወሓትን ጥለው የወጡ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ጉዳይንም በተመለከተ ሟቹ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስን በመደገፍና የእነስዬ አብርሃን ቡድንን በመንቀፍ በሰጡት አስተያየት መነሻቸው የኤርትራ ጉዳይ ይሁን እንጂ ዋና ዓላማቸው የሥልጣን ጥማት ነው ብለዋል፡፡ «የሥልጣን ጥማቱ ታምቆ የቆየ ነው፡፡ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የመውረሩን ጉዳይ ያለመከታተላችን የሁላችንም ድክመት ነው፡፡ ቀደም ብለን ማወቅ ነበረብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለሰላም አሟጠን ዕድል እንስጥ፣ ዕድሉ ካላዋጣን መዋጋት ማን ይከለክለናል የሚሉ የአመራር አባላት ነበሩ፡፡ እኛ ከኢሳያስ ተሸለን መገኘት አለብን፤ የእኛ ሰዎች ግን እንደ ኢሳያስ ሆኑ፡፡ ነፋስ በኤርትራ መጣ ከተባለ እንዋጋ ነው የሚሉት፡፡ ከወላጆቻቸው በምንም አይለዩም፡፡ ስንወረር ዝም ብላችሁ አያችሁ የሚለውን እንደምክንያት ወስደው ቡድን ፈጠሩ»ብለዋል፡፡
ተወልደ የህወሃት ምክትል ሊቀመንበር እያለ፣ ስዬም የመከላከያ ሚኒስትር እያለ ኤርትራ ነጻነትዋን ስታገኝ የአሰብ ወደብ ጉዳይ አብሮ ያለቀለት ነበር ያሉት አቶ ስብሃት፣ አሁን የአሰብ ጉዳይ እንደልዩነት የሚነሳው ሰበብ እንጂ ጉዳዩ ወንበር ፍለጋ ነው ሲሉ የእነስዬን ቡድን በሥልጣን ጥመኝነት ፈርጀዋል፡፡
ጡረተኛው አቶ ስብሃት በአሁኑ ወቅት እምብዛም እንቅስቃሴ የሌለውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የሠላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡