በምእራብ ሸዋ አንድ አባት የልጃቸውን የሙት አመት በማክበራቸው መታሰራቸው ታወቀ

የካቲት ፮(ስድስት) ቀን፳፻፯ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በአቡነ ግንደበረት ወረዳ በመንዲዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ባልቻ፣ በፌደራል ፖሊሶች በግፍ የተገደለባቸውን ደሜ ባልቻ የተባለውን ልጃቸውን የሙት አመት በመዘከራቸው፣ ለምን ይህን አደረጉ በሚል እርሳቸውና ሌሎች 10 ወጣቶች ባለፈው ሰኞ ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል።

አቶ ባልቻ የልጃቸው ገዳዮች እንዲያዙ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም አልተሳካላቸውም። የልጃቸውን ፎቶ ይዘው ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ሲያለቅሱ መታየታቸውን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣  የአካባቢውን ሰዎች ሰብስበው ለልጃቸው በማልቀስ ላይ ነበሩ።  በስፍራው የተገኙ ከ10 ያላነሱ የሟች ጓደኞች ተይዘው መታሰራቸውንና አመጽ በመቀስቀስ ወንጀል መከሰሳቸው ታውቋል።

አቶ ባልቻ የልጃቸው ገዳይ የሆነው የፌደራል ፖሊስ አባል እንዲያዝ ለወራት ከደከሙና ተስፋ ካጡ በሁዋላ የመጨረሻውን የማስታወሻ ዝግጅት ማዘጋጀታቸው ታውቋል። ተማሪ ደሜ ባልቻ የ12ኛ ክፍል ትምህርትን ማጠናቀቁን ተከትሎ ፣ የመሸኛ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በፌደራል ፖሊሶች መገደሉ መዘገቡ ይታወቃል።

በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን ፖሊስ አስተያየት ለማግነት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።