ጥር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በባህርዳር ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ ድልድዩ ሲሰራ አለሁ የመሰረት ዲንጋዩ ሲቀመጥ ነበርኩ ካሉ በኋላ ከ25 እስከ 30 ዓመት እንደሚያገለግል በይፋ ተነግሮ እንደተሰራ ከዚህ ዓመት በላይ ከቆየ አደጋ ለያደርስ እንደሚችል በወቅቱ በነበሩ የግንባታ ባለሙያዎች እንደተነገረ በማስታወስ ገልጸው ምንም አይነት የተሰራ አዲስ ነገር ሳይኖር ከ50 ዓመታት በላይ መቆየቱ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡
ከ47 ዓመት በፊት በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የነበሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ ለረዢም አመታት በድልድዩ የተመደቡ ተቆጣጣሪዎች የሚያልፉ መኪኖች ተራ በተራ እንዲጓዙ በማድረግ የድልድዩን ጤንነት ይጠብቁ የነበረው የጥበቃ አሰራር አሁን የለም፡፡ይህም በድልድዩ ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረጉ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት በቀበሌ ህዝባዊ ስብሰባዎች ብያቀርቡም ምንም ዓይነት በጎ ምላሽ አልተሰጠንም በማለት ተናግረዋል፡፡
የገዢው ፓርቲ በየጊዜው በህዝባዊ ስብሰባዎች የሚገባውን ቃል አለመጠበቁ እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች የየባህርዳሩ አባይ ድልድይ ከእድሜው መርዘም እና ስፋቱ መጥበብ የተነሳ ለልዩ ልዩ አደጋዎች በየጊዜው መከሰት ምክንያት ለእድሳት በሚል የከተማ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግስት የሚላከውን የእድሳት ገንዘብ ለግል ጥቀም ማዋላቸው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡