ጥር ፲፰(አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በትናንቱ የአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በፖሊሶች ከፍተኛ ብትር ያረፈበትና የአካል ጉዳት የደረሰበት ጋዜጠኛ ስለሽ ታሞ በተኛበት ከኢሳት ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ትናንት እንደሱ የከፋ በትር ላረፈባቸው የትግል አጋሮቹ እና ለለውጥ ሀይሎች በሙሉ፦<< አይዟችሁ!እንበርታ! መብታችንን ለማስከበር ከምናደርገው ትግል በፍጹም ወደ ሁዋላ እንዳንል፤ 2007 የለውጥ ዓመታችን ነው”ሲል መልእክት አስተላልፏል።
በሰልፉ ላይ እንዴት እና በምን እንደተመታ እንዲሁም መመታቱን ተከትሎ የሆነውን ነገር እንደማያስታውስ የተናገረው ጋዜጠኛ ስለሽ፤ ደብዳቢዎቹ ከላይ በታዘዙት መሰረት እሱንና የተወሰኑ አጋሮቹን ተመዳድበው ኢላማ ውስጥ ሳያስገቧችወ እንዳልቀረ ጥርጣሬ አለው።
ጓደኞቹ ወደ ሆስፒታል ወስደውት በተደረገ የራጅ ምርመራ በተለይ የእጆቹ አጥንቶች እንደተሰባበሩና ከፍተኛ ኦፕሬሽን መደረግ እንዳለበት በሀኪሞች የተነገረው ስለሽ፤የፊታችን ሐሙስ ኦፕሬሽን እስከሚደረግ ድረስ ለጊዜው በጀሶ ታጅሎለት ተኝቶ ይገኛል።
በእጁ ላይ ከደረሰበት ስብራት በተጨማሪ ፊቱን ጭምሮ በመላ አካሉ ላይ ከባድ ቅጥቀጣ ደርሶበታል። << ይሁንና ይህ ድበድባና ዱላ እኔን፣ ጓደኞቼንም ሆነ የለውጥ ሀይሎችን ከትግላችን አይገታንም>> ብሏል-ስለሽ
ነፍስ ጡሯን የፓርቲውን አባል ጨምሮ አንድነት ፓርቲ ትናንት እሁድ በቀበና በጠራው ሰልፍ ላይ የወጡ በርካታ ሰዎች በፖሊሶች ክፉኛ መደብደባቸውና ጥቂት የማይባሉ ታፍሰው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ይታወቃል።