መንግስት በካራቱሪ ኩባንያ እምነት ማጣቱን ገለጸ
ጥር ፲፩(አስራ አንድ ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካራቱሪ በበኩሉ መንግስት አስፈላጊውን ነገር አላመቻቸልኝም ባይ ነው።
የህንዱ ግዙፍ ኩባንያ <<ካሩቱሪ ግሎባል ሊሚትድ>> በኢትዮጵያ ሲያደርግ በቆየው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መንግሥት እምነት እንዳጣበት መግለጹን ሪፖርተር ዘግቧል።
አቶ አበራ ሙላት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኩባንያው ይጠበቅበት የነበረውን ሥራ ማከናወን ሳይችል ቀርቷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ እንደሚገልጹት፣ ካሩቱሪ ኩባንያ በገባበት አስተዳደራዊ ቀውስ ምክንያት ለኪሳራ ከመዳረጉም በላይ፣ ወደ መዘጋቱ እያዘገመ ነው።
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፤ ኩባንያውን በቦርድ የሚመሩት 19 ግለሰቦች ሲሆኑ፤ ለኪሳራ የተዳረገውም በመካከላቸው በተፈጠረ የአመራር ችግር ነው። ካራቱሪ ኩባንያ ግን ለኪሳራ የተዳረገው መንግሥት ለኢንቨስትመንት የሚመች ዕድል ስላልፈጠረ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ የሳል።
አቶ አበራ ይህን የኩባንያውን ቅሬታ አይቀበሉትም። ኩባንያው በራሱ ችግር ኪሳራ ላይ ወድቆ ሳለ የመንግስትን ስም ማጥፋት ተያይዟል ባይ ናቸው።
ኩባንያው በዝቅተኛ ገንዘብ ከተሰጠው የሊዝ መሬት ባሻገር በርካታ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ እንደተፈቀደለት አቶ አበራ ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም የፋይናንስ ችግሮች አጋጥመውትም ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቻ የተፈቀደውን የማሽነሪ ማከራየት ሥራ ለካሩቱሪ ብቻ ተፈቅዶለት ሲሠራ እንደነበር አቶ አበራ አስታውሰዋል፡፡
ካሩቱሪ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በሄክታር 20 ብር ወይም አንድ ዶላር ሂሳብ ከጋምቤላ ክልል 300 ሺሕ ሔክታር መሬት በሊዝ መውሰዱና ሁዋላ ላይ ከመንግስት ጋር በተደረገ ድርድር የመሬቱ መጠን ወደ አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር እንዲቀንስ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ከተለያዩ ባንኮች በብድር የወሰደውን 170 ሚሊዮ ብር እዳ በወቅቱ መክፈል ያልቻለው ካራቱሪ፤ በአሁኑ ወቅት በኪሳራ ሳቢያ የእርሻ መሳሪያዎቹን እስከማቅረብ ደርሷል።
ኩባንያው ከባንኮች ጋርም በብድር ዕዳ ምክንያት እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ መካረር ውስጥ መግባቱም ተመልክቷል።
2015-01-19