ታኀሳስ ፲፫(አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአየር ሃይል ምንጮች እንደገለጹት ሰሞኑን ኤም አይ 35 የተባለ የውጊያ ሄሊኮፕተር ይዘው በመጥፋት ወደ አልታወቀ ስፍራ የተጓዙት ሁለቱን አብራሪዎችና አንድ ቴክኒሻንን ለመፈለግ አየር ሃይል በተለያዩ አካበባዎች አሰሳ ሲያደርግ ቢቆይም በመጨረሻ ፍለጋው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ፍለጋው እንዲቋረጥ የተደረገበት ዋና ምክንያት አብራሪዎቹ ሆን ብለው መጥፋታቸውና ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በሰላም ወደአልታወቀ ስፍራ መሄዳቸውን የአየር ሃይል አዛዦች ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸው ነው።
ኢሳት መጀመሪያ ላይ በደረሰው መረጃ መሰረት የጠፉት 2 አብረራዎች መሆናቸውን መዘገቡ የሚታወስ ቢሆንም፣ ከአየር ሃይል የደረሰውን መረጃ መሰረት አድርጎ ባደረገው ማጣራት የጠፉት 2 አብራሪዎችና አንድ የበረራ ቴክኒሻን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችሎአል። ከፍተኛ የአብራሪነት ልምድ የነበራቸው ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ ከበረራ ቴክኒሻኑ ጸጋ ብርሃን ግደይ ጋር በመሆን ሄሌኮፕተሮቻቸውን በመያዝ የተሰወሩ ሲሆን፣ ሰዎቹ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሎአል።
ጉዳዩን በተመለከተ የአየር ሃይል ም/ል አዛዥ የሆኑትን ብርጋዲየር ጄኔራል ማሾ ሃጎስን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። ይሁን እንጅ አየር ሃይሉን እና ስምሪቶችን ከጀርባ ሆነው ይመሩታል የሚባሉት የድሬዳዋ አየር ሃይል ምድብ አዛዥ ኮ/ል አበበ ተካን በስልክ ለማነጋጋር ጥረት ያደርግን ቢሆንም፣ ኮሎኔሉ ከየት እንደምንደውል ከጠየቁን በሁዋላ የምንደውልበትን ቦታና ድርጅት ስንነግራቸው፣ ” ለእናንተ ደውለውላችሁ ነበርን ?” ብለው ከጠየቁን በሁዋላ፣ እኛ መረጃ ደርሶን እንደደወልንላቸው ስንገልጽላቸው ” ዝጋ ” ብለው ስልኩን ዘግተውታል። በዚሁ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃውን እየተከታተልን የምናቅርብ መሆኑን እንገልጻለን።