ታኀሳስ ፲፫(አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘጠኝ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያቀፈው ትብብር ባወጣው መግለጫ የባህርዳር ከተማዋ ነዋሪዎች ባዶ እጃቸውን ሆነው በሰላማዊ መንገድ ባሰሙት የተቃውሞ ድምጽ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን በወሰደው ዘግናኝና አሰቃቂ በጥይት የታገዘ የኃይል እርምጃ እስካሁን የአምስት ንፁኃን ዜጎች ህይወት መቅጠፉን አስታወሶ፣ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ አዛውንት እማሆይንና አካል ጉዳተኛ ጨምሮ በርካቶችን በማቁሰል የአካል ማጉደል ማድረሱ፣ በምንም መለኪያና ሁኔታ፣ የሞራል መከራከሪያ ሊቀርብለት የማይችል ህገወጥና ኃላፊነት የጎደለው ‹‹መንግሥት ነኝ›› ከሚል አካል የማይጠበቅ ዘግናኝ የአረመኔ ተግባር ነው ሲል ኮንኖታል።
የኃይል እርምጃው እስከዛሬ ‹‹ይህ መንግሥት የማን ነው፣ የቆመውስ ለማን ነው?›› ለሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ ‹‹የሥልጣኑና ለሥልጣኑ ብቻ ›› መሆኑን በግልጽ ያሳየበትና በህገ አራዊት ስለመመራቱ የማያሻማ ምላሽ የሰጠበት በመሆኑ፣ ትብብሩ እርምጃውን ከማውገዝ አልፎ፣ የተወሰደው እርምጃ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በሰጡ ባለሥልጣናትና እርምጃ በወሰዱት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲከፈል ጠይቋል።
ትብብሩ አያይዞም ገዢው ፓርቲ የተያያዘው የአፈና መንገድ ለጥያቄዎች መልስ ሊሆን ወይም ትግሉን ሊያቆም እንደማይችል በቅርቡ ከታየው ያለፈው ጁምኣ የቤኒ መስጂድ የሙስሊሞች ተቃውሞ ስልትና አተገባበር ተረድቶ ቆም ብሎ እንዲያስብና ለህዝብ ጥያቄዎች ጆሮውን፣ ለህዝብ ብሶት ልቡን ፣ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለህግ የበላይነት በሩን እንዲከፍት፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የእያንዳንዱ በር እስኪንኳኳ ሳንጠብቅ ይህን ዓይነቱን ኢ-ህገመንግሥታዊና አረመኔያዊ እርምጃ በአንድነት ቆመን እንድናወግዘውና እንድንታገለው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የአገርና ህዝብ ጉዳይ የበላይና ቀዳሚ ስለሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከትብብራችን ጋር በጋራ ለመስራት ትብብሩን እንድትቀላቀሉ የሚል ጥሪ አቅርቧል።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ታህሳስ 10/ 2007 ዓም ባወጣው መግለጫ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተወሰደውን እርምጃ አውግዟል።
ኢህአዴግ ቤተ እምነቶችን በየምክንያቱ መዳፈር የጀመረው ዛሬ አይደለም የሚለው አንድነት ከአሁን በፊት በሞስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የፈፀመው ግፍና የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ አሁን ደግሞ በባህር ዳር ከተማ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ላይ የወሰደው የኃይል እርምጃ ለሰው ህይወት መጥፋትና ለአካል መጉደል ምክንያት በመሆኑ እነዚህ ወንጀሉን የፈፀሙ፣ ያዘዙና ያስፈፀሙ አካላት በየደረጃው በህግ ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ ለማድረግ አስፈላጊውን ትግል እንደሚያደርግ አስታውቋል።