ታኀሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በጅማ ዞን ኤዳ ደሌ ቀበሌ ታዋቂ ቡና ነጋዴ የሆኑት አቶ ነፍሶ ላቫዥ ለዝርፊያ በሄዱ በአራት የፖሊስ አመራሮች ተገድለዋል።
አቶ ነፍሶ ጅማ ውስጥ ቡና ነግደው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ መንገድ ላይ አድብተው ይጠብቁዋቸው የነበሩት ፖሊሶች የያዙትን ገንዘብ እንዲሰጧቸው ሲጠይቋቸው ነጋዴው ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረቸው ፣ ሊያጋልጡን ይችላሉ በሚል ተኩሰው በመግደል ለማምለጥ ከሞከሩ በሁዋላ በህዝቡ ትብብር ተይዘዋል።
ገዳዮቹ ኢንስፔክተር ዋለልኝ፣ ኮንስታብል ሲሳይ እና ለጊዜው ማእረጋቸው ያልታወቀው የፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ወታደር ማሙሽና ወታደር ተመስጌን ናቸው። በፖሊሶች ድርጊት የተበሳጨው የቀበሌው ነዋሪ መሳሪያ በመያዝ ተቃውሞ ማሰማት ሲጀምር፣ በአካባቢው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ፣ የዞኑ አስተዳዳሪ ሰማን አባ ጉጂ፣ ከንቲባው አቶ ሶሎሞን እና የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው ኢ/ር ቃኘው የታያዙት ለፍርድ እንደሚቀርቡ በመግለጽ ህዝቡን ለማረጋጋት ሞክረዋል።