ታኀሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሙክታር ከድር ሰሞኑን ለክልሉ 5ሺ473 ፖሊሶች የሰጡት የማዕረግ ዕድገት መጪውን ምርጫን በመንግስት መዋቅር፣ በጀትና ጊዜ ተጠቅሞ ለማሸነፍ ኢህአዴግ የዘረጋው ስትራቴጂ አካል እንደሆነ ታዛቢዎች ተናገሩ፡፡
መጪው ምርጫ ሊካሄድ አምስት ወራት ብቻ በቀሩት በዚህ ጊዜ የማእረግ እድገት በብዛት መስጠት ለምርጫ ከሚሰጥ የጉቦ ቀብድ ተለይቶ አይታይም ያሉት ሰማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ምሁር በዚህ መልክ የምርጫ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚደረግ ሩጫ ህገወጥ ነው ብለውታል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በቅርቡም ለመከላከያ አባላቱ ተመሳሳይ የማዕረግ ዕድገት የሰጠ መሆኑን ያስታወሱት እኚሁ ምሁር ማዕረግ ለሚገባው መስጠት ተገቢነቱ አጠያያቂ ባይሆንም የምርጫ ወቅት ጠብቆ ማድረግ ግን ኢፍትሐዊ ምርጫን ለማካሄድ ከማሰብ ጋር በቀጥታ ይገናኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለምርጫ ቀብድ የሚሆኑ በአዲስአበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ለማውጣት፣ የአዲስአበባን ቀላል ባቡር አግልግሎት ለማስጀመር እየጣረ መሆንን ታዛቢዎች ጠቁመው እነዚህ ሁሉ አድራጎቶች የምርጫን ስርኣት የሚያዛቡ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳና ደጋፊ የማሰባሰብ አካሎች ናቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 40ኛ ዓመት ከየካቲት 11 ቀን በፊት ለማክበርና ሕዝቡ በህወሃት መስዋዕትነት ነጻ መውጣቱን ደጋግሞ ፕሮፖጋንዳ ለመስራት እንዲመች ህወሃት የጋበዛቸው አርቲስቶችና ጋዜጠኞች የፊታችን ሰኞ ወደትግይራ ክልል የሚጉዋዙ ሲሆን ይህም በመንግስት ወጪ የሚደረግ ቅስቀሳ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የምርጫ ዘመቻ አካል ነው ብለውታል፡፡