ታኀሳስ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ቤት ቢቀርቡም ሌላ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
7ተኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን የሰጠው የተከሳሽነት ቃል ከክሱ ጋር ተያይዞ ለጠበቃው ባለመቅረቡ ጠበቃው መቃወሚያቸውን እንዲያስገቡ ፍርድ ቤቱ ያዘዘ ሲሆን ፣ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾች በ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ በማድረግ ለማሸማቀቅ እየሞከሩ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን ተቀብሎ በቀጣይ ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ስለጉዳዩ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በሰላማዊ ታጋዮች ላይ ቀረበው ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው በሚል በሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሲተች ቆይቷል። በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና ጸሃፊዎች በመጪው ምርጫ ላይ ተጽእኖ ያሳርፋሉ በሚል ፍርሃት እንዲታሰሩ መደረጉን የሚጠቅሱት እነዚህ ድርጅቶች፣ መንግስት የጸረ ሽብር ህጉን ተቃዋሚዎችን ለመምቻነት እያዋለው በመሆኑ እንዲቀየር ይጠይቃሉ።
በሌላ ዜና ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው ወጣት ኢያስፔድ ተስፋየ ከሚሰራበት ንግድ ባንከ ታግዷል። ኢያስፔድ ለኢሳት እንደገለጸው ህዳር 27 በአዲስ አበባ ለማድረግ ታስቦ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተይዞ ለ6 ቀናት ያክል በእስር ቤት ካሳለፈ በሁዋላ ፣ ወደ ስራው ሲሄድ መታገዱ ተገልጾለታል።