ታኀሳስ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባንኩ እንደሚለው በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው አገሮች ቅርንጫፎችን በመክፈት በአመት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን፣ ከባንክ ውጭ የሚደረገውን ገንዘብ የማስተላለፍ ዘዴ ለመቆጣጠር አስቧል። አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና ሳውድ አረቢያ በመጀመሪያው ዙር የንግድ ባንኮች ቅርንጫፎች ከሚከፈትባቸው አገራት ተርታ ተመድበዋል። ባንኮቹ መከፈታቸው ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለመጨመር እንደሚረዳም ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ምርት ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ይልቅ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የምታገኘው ገቢ እየበለጠ ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በንግድ ባንክ ገንዘብ ሲልክ መረጃዎቹ ለመንግስት የሚሰጡ በመሆናቸው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ከባንክ ውጭ ባሉ መንገዶች ለማስተላለፍ ይመርጣሉ። በጸረ ሽብር አዋጁ መሰረት አንድ ሰው እስከ 200 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ካስተላለፈ፣ የአስተላላፊው መረጃ ጸረ ሽብር ግብረሃይል ጋር መድረስ አለበት። አንዳንድ መንግስትን የሚቃወሙ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በንግድ ባንክ በኩል ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በሚያስተላልፉበት ጊዜ ቤተሰቦቻቸው በደህንነት ሃይሎች እየተጠሩ እንደሚጠየቁ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።