በፓኪስታን-ፔሽዋር  ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት በተከፈተ የአሸባሪዎች ጥቃት በትንሹ 126 ስዎች መገደላቸው ተሰገበ።

ታኀሳስ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደሰገበው በታሊባን የተፈጸመ ነው በተባለው በሲህ ጥቃት ከሞቱት መካከል በርካታዎቹ ህጻናት ናቸው።

ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ አምስት ወይም ስድስት የሚሆኑ ታጣቂዎች ወደ ትምህርት ቤቱ መግባታቸውን የትናገሩት ባለስልጣናቱ፤ ወዲያውኑ አካባቢው በደህንነቶች እንዲከበብ መደረጉን ተከትሎ የተኩስና የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ተናግረዋል።

ወደ 500 ከሚጠጉ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በርካቶቹ ማምለጣቸውን የጠቀሱት ባለስልጣናቱ፤ይሁንና  ምን ያህል ተማሪዎች በታጣቂዎቹ ታግተው እንደሚገኙ  ለማወቅ አለመቻሉ ገልጸዋል።

ጥቃቱ፤ በፓኪስታን በሽብርተኞች ከተፈጸሙ  ከባድ  ጥቃቶች  አንዱ  ነው ተብሏል። የቢቢሲው  አመር አህመድ ከኢስላማባድ እንዳጠናቀረው ሪፖርት  ፈጽሞ ያልተጠበቀው የህጻናት ተማሪዎች ግድያ  ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።

በታሊባን ሚሊሻዎች  አመጽ  ባለፉ ጥቂት ዓመታት ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፓኪስታናውያን ህይወታቸውን አጥተዋል። የታሊባን ሚሊሻዎች ቃል አቀባይ  በሰጠው መግለጫ  በትምህርት ቤቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት- የፓኪስታን ሰራዊት በታሊባን ላይ እየወሰደ ላለው እርምጃ   አጸፋዊ ምላሽ  ነው ብሏል።.

በቅርቡ በሰሜን ዋሲርስታን እና በካይበር አካባቢ  የፓኪስታን ሰራዊት በከፈተው ሰመቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሊባን ሚሊሻዎች መገደላቸው ይታወሳል።