ኀዳር ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ ላይ አንድ ከተማ ውበቱ የተባለ ሰው ሃብታሙ ሺበሺ የተባለን ሰው መግደሉን ተከትሎ፣ ገዳይን ለመያዝ በተደረገ ጥረት ሰኞ ህዳር 29፣ 2007 ዓም በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።
ከተማ ውበቱ የተባለው ሰው በ1999 ዓም የሰዎች ለሰዎች የተባለውን ድርጅት ገንዘብ ከዘረፈ በሁዋላ ሃይማኖት ሺበሺ በተባለው ግለሰብ ቤት በአደራ ማስቀመጡን ተከትሎ ሃይማኖት ሺበሺ ገንዘቡን መካዱን የሚናገሩት የአካባቢው ሰዎች፣ ከዚህም በላይ ሃይማኖት ገንዘቡን አካፍልሃለው ብሎ ከተማ ውበቱን ከቀጠረው በሁዋላ
በጥይት አቁስሎታል።
ከተማ ውበቱ በቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ በዝርፊያ ተከሶ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በ2003 ዓም ሃይማኖት መኪና ላይ ሊሳፈር ሲል መግደሉንና በመኪናው ዙሪያ የነበሩ 2 መምህራንና አንድ ሌላ ተሳፋሪ መሞታቸውን አክለዋል።
የሃይማኖት ወንድም የሆነው ሃብታሙ ሺበሺ እንዲሁም የሟቹ የቅርብ ዘመድ የሆኑት የፓርላማ አባሉ አቶ ለማ ተሰማ፣ አቶ ከተማ ውበቱን ለማስያዝ ላለፉት 4 ዓመታት ሲከታተሉት ቢቆዩም፣ ከተማ ውበቱና ደጉ አቢ የተባለ ግብረአበሩ፣ ሃብታሙ ሺበሺን ጉንዶ መስቀል ላይ ትናንት በጥይት ገድለውት አምልጠዋል።
ገዳዮችን አድነው ለመያዝ የወረዳው ፖሊስ አባላት፣ የወረዳው የሚሊሺያ አባላትና የዞን አድማ በታኞች አሰሳ ያደረጉ ሲሆን፣ ካቢ ቀበሌ ውስጥ መሽጎ የነበረውን ደጉ አቢን አራት የእጅ ቦንቦች በመወርወር ሲገድሉት፣ ከከተማ ውበቱ ጋር ደግሞ ለረጅም ሰአታት የቆየ የተኩስ ለውውጥ ተካሂዷል።
በተኩስ ልውውጡ መሃል የአድማ ብተና ሃላፊው ሲገደል አንድ ሌላ ፖሊስ ደግሞ በጽኑ ቆስሎ ሆስፒታል ተኝቷል። ገዳዩ ከተማ ውበቱም ከሌሊቱ 11 ሰዓት መገደሉን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።