ኀዳር ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የምርጫ ስርዓት ለውጥ እንዲደረግ ለመጠየቅ ህዳር 27 ቀን የአዳር ተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ወደ አደባባይ በወጡት 9 የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ድብደባ በመፈጸም ወደ እስር ቤት ቢወስዱዋቸውም፣ የትብብሩ አመራሮች ግን ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያውያን ለትግሉ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሶስተኛ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚገኙት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ኤርጫፎ ኤርዳሎ፣ አለሳ መንገሻና ሌሎችም አመራሮች አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፣ በጨርቆስ ታስረው የሚገኙት እነ አቶ ግርማ በቀለ ደግሞ የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
አመራሮቹ ሀግመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድና የተከለከለ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ታውቋል።
በፍርድ ቤት አካባቢ ሆነው ጉዳዩን ከተከታተሉት መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ ለኢሳት ሲናገር፣ አብዛኞቹ አመራሮች ሲሄዱ ያነክሱ እንደነበር ገልጾ፣ ኢ/ር ይልቃል እጁ አካባቢ መመታቱን፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ ደግሞ እጅና እግሩ አካባቢ በጨርቅ ተጠቅሎ ማየቱን ገልጿል። ሴት እስረኞችም ሲጓዙ ያነክሱ እንደነበር በተለይ አንደኛዋ ኩላሊቷ አካባቢ መመታቱዋን እንደገለጸችለት ተናግሯል ሴት እስረኞችን ለመጠየቅ በሄደበት ወቅት ለአጭር ደቂቃዎች ራቅ ብሎ ለማናገር መቻሉን የገለጸው ዮሴፍ ተሻገር በበኩሉ፣ ሴቶች በጠንካራ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
ኮተቤ አካባቢ ታስረው ስለሚገኙት የድርጅት መሪዎችና አባላት ጉዳይ በስፍራው በመገኘት ለመታዘብ የቻለው አቶ እምላሉ ፍሰሃ እንደገለጸው ደግሞ ምንም እንኳ እስረኞቹ መጸዳጃ ቤት አካባቢ በመታሰራቸው እንዲሰቃዩ ቢደርግም አሁንም በጠንካራ መንፈስ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
መንግስት የወሰደው እርምጃ በትብብሩ የወደፊት የትግል አካሄድ ላይ ተጽአኖ ይኖረው እንደሆን የተጠየቁት የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙዲሰር ሲመልሱ ” መንግስት እስረኞች ይፈቱ አይፈቱ ወደ ሚል አታካራ እንድንገባ ቢፈልግም፣ እኛ ግን ትግሉን ወደ ፊት ከመግፋት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለትግሉ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አቶ ኑሪ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ፓርቲ በ9 ፓርቲዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አውግዟል። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ” የዘጠኙ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድርግ መብት ከመጠቀም ውጪ ያጠፉት ምንም ዓይነት ነገር ስለሌለ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል።” ብሎአል። ፓርቲው ” የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ህገወጥና አረመኔያዊ ድርጊት በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፤ ኢህአዴግን በቃህ ሊለው ይግባል።” በማለት በመግለጫው አስታውሷል።