ከኢቲቪ ዋና ሥራአስኪያጅነት በአቅም ማነስ ተሰናብተው ለማካካሻ ወደ ኢትዮጽያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተመደቡት አቶ ዘርዓይ አስገዶም በብሮድካስት ባለስልጣን የህትመት ድርጅቶች የሚገቡት አስገዳደጅ ውል በማዘጋጀት በግዴታ በማስፈረም ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡

ኀዳር ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ባለስልጣኑ አሳታሚዎች ዓመታዊ የንግድ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ወደንግድ ሚኒስቴር ሲሄዱ በየዓመቱ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ የሚገደዱ ሲሆን የሙያ ብቃቱን ለማግኘት ባለፉት ወራት ወደብሮድካስት ባለሰልጣን የሄዱ አሳታሚዎች ያልጠበቁትን ግዴታ እነዲገቡ የሚቃወሙ ከሆነ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት እንደማይሰጣቸው በተነገራቸው መሠረት አብዛኛዎቹ ተገደው ፈርመዋል፡፡

በንግድ ምዝገባ ፈቃድ መስጫ መደብ ቁጥር 89 ሺ 510 የጋዜጣና መጽሔት አሳታሚ የምዝገባ ምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው ሰዎች ከሚፈርሙዋቸው ግዴታዎች መካከል ” የተሟላ የሥራ ሪከርድ እና ሰነዶች አደራጅቼ እይዛለሁ፣ ለምርመራ ሲፈለግም ለባለሰልጣኑም ሆነ ለሚመለከታቸው ሕጋዊ አካል የማቀርብ መሆኔን አረገጋግጣለሁ”  የሚል ይገኝበታል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጁ ቁጥር 590/2000 አክብሬ አስራለሁ የሚልም ተከታይ አስገዳጅ ውል ውስጥ ሰፍሮአል፡፡

አሳታሚዎች በተለይ “ሰነድ አሳያለሁ፣ ሪከርድ እይዛለሁ” የሚለው አስገዳጅ አንቀጽ ከባለስልጣኑ ሥልጣን ውጪ የሆነና የፕሬስ ነጻነትን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ አሳታሚዎቹ በሥራ ላይ ያለ አዋጅ አክብሮ መሥራት የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ እንደገና በውል አከብራለሁ የሚል አስገዳጅ ፊርማ ለምን እንደተቀመጠ ግራ እንደገባቸው፣ ምናልባት አሳታሚዎች ተሸማቀው በጋዜጣና መጽሔት ይዘቶቻቸውን ምንም ዓይነት የተቃውሞ ጽሑፍ እንዳያስተናግዱ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በዚሁ አስገዳጅ ውል አንቀጽ 9 ላይ «ከባለለስልጣኑ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ስወስድ የመረጥኩትን ይዘት ከባለለስልጣኑ ዕውቅና ውጪ ለውጥ ባደርግ እና የብቃት ማረጋገጫ መስፈርቱን መሰረት የህትመት ሥራዬን ባላከናውን የተሰጠኝ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ሊሰረዝብኝ እንደሚገባ ተስማምቼ ይህን የውል ግዴታ መግባቴን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ» የሚልም ሰፍሯል፡፡ ይህ አንቀጽ ምናልባትም እነ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመሳሰሉ ጋዜጠኞች አንዱ ሕትመት ሲዘጋባቸው በሌላ ህትመት ብቅ የማለታቸው ልምድ ሌሎችም እንዳይከተሉት  ለመዝጋት ሆን ተብሎ የተቀመጠ ሊሆን እንደሚችል ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የመንግስትን ኢፍትሃዊ አሰራሮችን በድፍረት በመዘገብ የሚታወቁት ጋዜጦች ከመንግስት በሚደርስባቸው ጫና እንዲዘጉ መደረጉ ይታወቃል። በርካታ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ሲገኙ ብዙዎቹ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል።