በትግራይ፣ አማራ ክልሎች የሃይማኖት መሪዎች የተሰጣቸውን የደህንነት ስራ በትክልል አልሰሩም በሚል ተተቹ

ኀዳር ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ባዘጋጀው የ2006 የጸጥታ የደህንነት ግምገማ ላይ የተገኙ የተለያዩ ክልሎች የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች ባቀረቡት ሪፖርት በአዲስ አበባ የሃይማኖት አባቶች የተሰጣቸውን የደህንነት ተልእኮ በፈቃደኝነት አምነው ሲፈጽሙ በትግራይና ፣ በአማራ ክልሎች ግን የሃይማኖት አባቶች ተልእኮዋቸውን በአግባቡ ሳይወጡ ቀርተዋል።

የትግራይ ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ እንደተናገሩት በክልሉ አብዛኛው ህዝብ የኦሮቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ቢሆንም፣ የሃይማኖት አባቶች ሽማግሌዎች በመሆናቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ እንደ ፌደራል የሃይማኖት አባቶች በአግባቡ እንደማይፈጽሙና ከአመራሩ መመሪያ የሚጠብቁ የራስ ተነሳሽነት የሌላቸውና የአቅም ውስንነት ያላቸው ናቸው ብለዋል።

ይህንኑ ሃሳብ የአጠናከሩት የአማራው ክልል የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደሴ አሰሜ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን ከክልል እስከወረዳ ለማደራጀት ቢሞከርም ተነሳሽነት በመጥፋቱ የታሰበው ሊሳካ አለመቻሉን ገልጸዋል። በተለያዩ ቦታዎች መስኪዶችን ከአክራሪዎች እጅ እየነጠቁ ለመጅሊሱ ማስረከባቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል ። በኦሮምያ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ ደግሞ የፌደራል መጅሊስ አመራሮች መከፋፈላቸውን ገልጸው፣ ክፍፍሉ እስከታች በመውረዱ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሄ መውሰድ ይገባል ብለዋል

በአዲስ አበባ 7ቱም የሃይማኖት ተቋማት ለመንግስት የደህንነት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወቃል።