ኀዳር ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትብበሩ የንግዱ ማህበረሰብ ህዳር 27/28 2007 ዓ.ም በሚደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከመሳተፍ ጀምሮ በገንዘብና በሌሎችም መንገዶች ድጋፉን እንዲገልጽ ጠይቋል።
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ ጀምሮ ነጻ ገበያን እንደሚከተል በመግለጹ የንግዱ ማህበረሰብ በነጻ ገበያ መርህ ተወዳድሮ ራሱንም አገሩንም ይጠቅማል የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም ይህ ተስፋ እውን ሳይሆን መቅረቱን የገለጸው ትብብሩ፣ ይልቁንም ገዥው ፓርቲ የራሱን የኢኮኖሚ ኢምፓየር በመመስረት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ማበላሸቱን ገልጿል።
ግልጽነት በጎደለው መንገድ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት እየተጠቀሙ ከሚገኙት የገዥው ፓርቲ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር መወዳደር አቅቷቸው የከሰሩት በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸውን የገለጸው የ9 ፓርቲዎች ትብብር፣ በተለያየ መንገድ አሁንም ድረስ የቀጠሉትም ቢሆን ከገዥው ፓርቲ ተቋማት ጋር መወዳደር ተስኗቸው ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ማበርከት የነበረባቸውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ ተደርገዋል ብሎአል።
የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ” ለገዥው ፓርቲ ባለማደራቸው ምክንያት አግባብ ያልሆነ ቀረጥና ሌሎች ጫናዎች እየተጣሉባቸው አንድም ከገበያ ወጥተዋል፡፡ አሊያም የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘትና አገራቸውን መጥቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል” የሚለው ተብብር፣ ነጋዴዎች በተለያዩ ጊዜያት ለገዥው ፓርቲ መዋጮ እንዲከፍሉ ከመጠየቃቸውም በላይ ስርዓቱ ባነገሰው ሙስና ምክንያት እጅ ተወርች ተይዘው ራሳቸውን፣ ህዝባቸውንና ለአገራችን ዴሞክራሲ ግንባታ ያበረክቱትን የነበረው አስተዋጽኦ እንዲገደብ ተድርጓል፡፡
ትብበሩ ህዳር 27/28 2007 ዓ.ም በሚያደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ የንግዱ ማህበረሰብ ትግሉን በመቀላቀል፣ በገንዘብና በሞራል በመደገፍ የዚህ ታሪካዊ ትግል አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል። ሰላማዊ ሰልፉ ኢትዮጵያውያን መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ጮራ የሚፈነጥቅ ነው ብሎ እንደሚያምን ትብብሩ በመግለጫው ማጠቃላይ አስፍሯል።
በተመሳሳይ ዜናም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ህግ አውጭውና ህግ አስፈጻሚው አካል የዜጎችን መብት እንዲያከብር በደብዳቤ መጠየቁን የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ትብብሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና ለአፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ እየተጣሱ የሚገኙትን የዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብት እንዲያከብሩ የሚጠይቁ ደብዳቤዎችን ማስገባቱን ኢንጅነር ይልቃል ለጋዜጣው ተናግረዋል።
9ኙ ፓርቲዎች በትብብር መስራት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ የመንግስት ተቋማት እየፈጸሟቸው የሚገኙትን ህገ ወጥ እርምጃዎች በመጥቀስ ህግ አስፈጻሚውና ህግ አውጭው እየተፈጸመ ለሚገኘው ህገ ወጥነት መፍትሄ እንዲሰጡና የዜጎችን መብት እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
‹‹መብቱን የተነፈገና ሠላማዊ እንቅስቃሴው በታፈነ ህዝብ ውስጥ በሚፈጠር ብሶት በማንኛውም ጊዜ ማናችንም ወደማንቆጣጠረው ህዝባዊ አመጽ ሊሸጋገርና አላስፈላጊ ግጭትና አለመረጋጋት በማስከተል በአገር ሃብት ውድመት፣ በህዝብ አካልና ህይወት አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡›› ሲል ተብብሩ በደብዳቤው ማስጠንቀቁን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደህንነትና ፖሊሶች የታፈነው የመኢአድ አመራር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የሰሜን ጎንደር አመራር የሆነው አቶ ችሎት ባዜ መስከረም 2/2007 ዓ.ም በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ከታፈነ በሁዋላ በወቅቱ ቤተሰቦቹ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንደተዛወረ መረጃ ቢደርሳቸውም ከማእከላዊ እስር ቤት ግለሰቡ እንደሌለ ተነግሯቸዋል፡፡
ቤተሰቦቹ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከሆነ በሚል ሪጂስትራር ላይ ስሙ እንደሰፈረ ቢያስጠይቁም እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ማረጋገጣቸውን ለጋዜጣው ገልጸዋል።
ከየክፍለ ሀገሩ በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ታፍነው በአሁኑ ወቅት ማዕከላዊ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የመኢአድ አመራሮች አራድ ምድብ ችሎት ቀርበው ለታህሳስ 21/2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ከግንቦት7 እና ከአርበኞች ግንባር ጋር በተያአዘ እንደሚከሰሱ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ከምእራብ አርማጭሆ ተያዙት እነ አቶ አንጋው ተገኝና አባይ ዘውዱ ለግንቦት7 የሰው ሃይል በመመልመል ወንጀል እንደሚከሰሱ ምንጮች ጠቅሰዋል። ሌሎችም በተመሳሳይ ከአርበኞች ግንባርና ግንቦት7 ጋር በቅንጅት ይሰራሉ በሚል ክስ እየተዘጋጀባቸው ነው።