ኀዳር ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትብብሩ ህዳር 27 እና 28 በመስቀል አደባባይ ለሚደረገው የአንድ ቀንና ሌሊት የተቃውሞ ሰልፍ ህዝቡ የተጀመረውን የሰው በሰው ቅስቀሳ እንዲደግፍ፣ የገንዘብ የሞራልና ቁሳቁስ ድጋፎችን እንዲያደርግ እንዲሁም ለትግሉ ይጠቅማል ያሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ህዝቡ በዝግጅቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በመስቀል አደባባይ በሚኖረው ቆይታ የሚያስልጉት ቁሳቁሶች በተለይም ደረቅ ምግብና ውሃ ከአሁኑ እንዲያዘጋጅ ትብብሩ አስታውሷል።
ትብብሩ ለመምህራን ባቀረበው ጥሪ ደግሞ፣ መምህራን በአንድ አገር ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማጋለጥና ህዝቡንም ለማንቃት ካላቸው ተደራሽነት እንዲሁም የሙያ ግዴታ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ታሪካዊ ግዴታችሁን ተወጡ ብሎአል።
“ህዳር 27/28 በተጠራው የአዳር ሰልፍ በመሳተፍና በሙያም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች የምታገኙዋቸውን ኢትዮጵያውያን በመቀስቀስ ጥሪውን እንዲቀላቀለሉ በማድረግ ግንባር ቀደሙን ሚና ” ተወጡ ሲል ትብብሩ ለመምህራን ጥሪውን አቅርቧል።
የ9ኝ ፓርቲዎች ትብብር የጠራው ተቃውሞ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ማግኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።