መንግስት ከጸጥታ ችግሮች መካከል የተወሰኑትን መቅረፉን አስታወቀ

ኀዳር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ከፌደራልና ከክልሎች ለተውጣጡ የጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች እንደተናገሩት መንግስት አራት የጸጥታ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ የመጀመሪያው የሽምቅ ውጊያ የሚያደርጉ ሃይሎች የፈጠሩት ስጋት ነው ያሉት ዶ/ር ሽፈራው እነዚህን ሃይሎች እና ሽብርተኞችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ፈተና መሆኑን ሲገልጹ፣ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የአክራሪነት አደጋ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መቻሉንም ተናግረዋል። በብሄሮች መካከል የሚታየውን ግጭትም ለመቆጣጠር መቻሉንና አፋርና ሶማሊን ለማስታረቅ የሚደረገው ጥረት ጥሩ ጅምር ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም እንዲሁ አክራሪነትን የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ለመቆጣጠር ቢቻልም የኤርትራ መንግስት እያስታጠቀ የሚልካቸው ሃይሎች አሁንም አደጋ እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል