ኀዳር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የገዢው መንግስት በምርጫ 2007 ያለውን ተቀባይነት ለማጠናከር በማሰብ የተለያዩ የህብረተሰቡን ክፍሎች በየክፍለ ከተማው በማሰባሰብ የተሰሩ ስራዎችን በማቅረብ ለመመስገን ሙከራ ቢያደርግም፤ተሰብሳቢዎች ግን ምንም እንዳልተሰራና ተሰራ የተባለውም ችግር ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የመንገዶች መበላሸት ያሳሰባቸው ነዋሪዎች በአካባቢው ላሉ አመራሮች የስራውን የጥራት ጉድለት ቢያሳውቁም የተስተካከለ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ “በ2006 የተሰራው ስራ በሙሉ ዜሮ ነው፡፡ በየክፍለ ከተማው ያለው የሰራተኛ ቁጥር ከ 8 ወደ 102 እንዳደገ ብትነግሩንም ለኛ የተረፈን የባለስልጣን ጋጋታ እንጅ የህዝቡን ስራ የሚሰሩት በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜየችሁን በስብሰባና የፖለቲካ ስራ በመስራት ታሳልፋልችሁ ” በማለት የተሰራው ስራ ለፖለቲካ ትረፍነት እንጅ ለህዝብ ተብሎ እንዳልሆነ የተናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ሌላው ቅሬታ አቅራቢ በአሁኑ ሰዓት ያሉ የኮብል ስቶን ስራዎች የመኪና ጎማ የሚደበድቡ ጥራት የሌላቸው በመሆናቸው በመንገዶች ዙሪያ የሚሰሩት የተፋሰስ ስራዎች ሁሉ ጥራታቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በኮብልስቶን አሰራር የሚታዩ የጥራት ችግሮች ከአመት ወደ አመት እየተባባሱ ቢሄዱም ባለፈው አመት የሚታዩ ችግሮችን በመነጋገር መሻሻል ያለባቸውን ያፈጻጸም ችግሮች ሲቀረፉ እንዳልታዩ ና የሚበላሹ መንገዶችን የማስተካከል ስራ ሲሰራ እንደማይታይ የሽምብጥ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡
“በመንገድ ስራው መስክ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ጊዜያዊ እንጅ የወደፊቷን ባህር ዳር እድገት ያማከለ አይደለም ” ያሉት የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ራዕይ የሌለው አመራር መሆኑንንና ስራው ራሱ እንደሚመሰክር ተናግረዋል፡፡
“በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች ስራ ተሰርቷል ወይ ካላችሁ መልሳችን አልተሰራም ነው፡፡”በማለት የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢ የህዳር 11 ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ለከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡“እንዲያው እንመሰጋገን ካልተባለ በስተቀር የተሰራ ስራ አለ ለማለት አያስደፍርም” በማለት በአሁኑ ሰዓት በመንገድ ልማት የሚሰሩ ስራዎች ነገ የሚፈርሱ በመሆናቸው የይድረስ ይድረስ ስራዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በባህር ዳር ከተማ የሚሰሩ የኮብልስቶን ንጣፍ ስራዎች በህዝብና ከተማ አስተዳደሩ መዋጮ ቢሰሩም መንገዶች በየቦታው ተጀምረው ሳይጨረሱ ወራትን በማስቆጠር በህብረተሰቡን ላይ ችግር ከመፍጠራቸው በላይ የንግድ ቤቶች በአግባቡ እንዳንሰራ እያገዱን ነው በማለት ያማርራሉ፡፡
ድንጋይ አንጣፊዎች ማሕበራት በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ማቅረብ ያለበትን የደቃቅ ዲንጋይ አቅርቦት ስለሚያዘገይ ስራው እንዲጓተት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡